ዛሬ ለምን ሰላማዊ ታጋይ ሆንኩ? የሰልጣን ምንጩ የህዝብ ድምፅ ሳይሆን የመሳሪያ ድምፅ
በሆነበት ሃገር ለምን ከዲሞፍተር መፈክርን መረጥኩ? ለምን ከጦር ግንባር ይልቅ አደባባዮችን መረጥኩ? ለምን እሾክን በሾክ ብዬ
በወጡበት መንገድ ለማውረድ ከመስራት ተቆጠብኩ? ፈሪ ስለሆንኩ? ቁርጠኝነቱ እና ፅናቱ ስለሌለኝ? ሞትን ስለምፈራ? ስል እራሴን
ጠየኩ፡፡ መልሱን ከስቃዬ ጀርባ አገኘሁት፡፡ ‹‹ደስ የሚል ስቃይ››

መሳሪያ አንስቼ ጫካ ያልገባሁት ሞትንም ስለምፈራም አይደለም፡፡ ስለሃገራዊ እና ስለ
ህዝባዊ አላማ መሞት በማይጠፋ ልደት መወለድ መሆኑን ከታሪክ በሚገባ ተምሬያለሁ፡፡ ስለ አፄ ቴዎድሮስ እና ስለ አፄ ዩሐንስ ስናስብ
ምናቸው ነው ትዝ የሚለን? ቴዲ በመቅደላ እንዲሁም ዩሐንስ በመተማ ስለ ሃገራቸው የከፈሉት መሰዋዕትነት አይደለምን? እንዚህ ጀግኖች
የሞቱበት ቀን ለማይጠፋ ልደት የተወለዱበት ቀን ነው፡፡ ታዲያ ለምንም ሞትን እፈራለሁ? በህይወት ለመኖር ምን ያጓጓኛል?
እኔ የሰላማዊ ትግልን የተቀላቀልኩት የምሞትለት ህዝብ እንጂ የምገለው ጠላት ስለሌለኝ
ነው፡፡ እኔ ነፍጥ አንስቼ ያልታገልኩት ወያኔ የምትባል አይጥ ህዝቡን እና ታሪኩን ስታነክተው ሳልመለከት ቀርቼ ሳይሆን ‹‹ምእንቲ ዛ ምጎጎ እታ አንጭዋ ትሕልፍ›› እንዳለችው የትግሬዋ
እምቤት ሆኖብኝ ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው…ባልና ሚስት አይጥ አስቸገረቻቸው፡፡ ዱላ አንስተው የቤቱን እቃ ሁሉ ገለባብጠው አይጧን
ማሳደድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሲሏት በዚያ፣ በዚያ ሲሏት በዚህ እያለች ብዙ አደከመቻቸው፡፡ በመጨረሻም አይጧ ዘላ ምጣዱ ላይ ቁጭ ማለቷን
የተመለከተችው ሚስት በአግራሞት ቆማ መመልከት ጀመረች፡፡ አይጧን ከምጣዱ ነጥላ ለመምታት አሰበች ግን አልቻለችም፡፡
ባል የሚስቱን መቆም ተመልክቶ ‹‹ምነው ትቆሚያለሽ አትያትም ወይ?›› አላት፡፡ ብልኋ
ሚስትም ‹‹መምታቱ አያቅትም ነገር ግን "ምእንቲ ዛ ምጎጎ እታ አንጭዋ ትሕልፍ"›› አለች ይባላል፡፡ ትርጉሙም
ስለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ ብዬ ነው ማለቷ ነው፡፡ በትጥቅ
ትግል ወቅት ስለሚፈርሰው ህንፃ እና መሰረተ-ልማት ሳይሆን ወድ ደሙን ስለሚያፈሰው እና መተኪያ አልባ ህይወቱን ስለሚሰዋው ወገኔ
አሰብኩ፡፡ እምቤቲቷ የአይጧ ጉዳት ምጣዱን ከመስበር ጋር አወዳድራ ትለፍ ብላለች፡፡ እኔም ሃገርን እና ስርዓቱን አወዳድሬ ሀገር
እና ህዝብን በማይጎዳ መልኩ ስርዓቱን ማስወገድ የሚያስችል ሁነኛ መንገድ ስፈልግ ከሰላማዊ ታግል እና ታጋዮች ጋር ተገናኘሁ፡፡
ስለዚህም እኔ ሰላማዊ ትግልን አምኜ ስቀላቀል
ስርዓት አልባው ስርዓት
እስር
ቤት
እንዳላው
ሳለውቅ
ቀርቼ
አይደለም፡፡
ወያኔ
መሳሪያ
እንዳላው
ሳለውቅ
ቀርቼ
አይደለም፡፡
ወያኔ
አሰቃይቶ ሊገድለኝ እንደሚችል
ሳለውቅ
ቀርቼ
አይደለም፡፡
የአገዛዝ ስርዓቱ
በቁሜ
ቆዳዬን
ገፎ
እንደ
በቆሎ
ሊቀቅለኝ
የሚያስችል ጭካኔ እንዳለው
ሳላውቅ
ቀርቼ
አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር አውቃለሁ፡፡ ከማዕከላዊ
እስከ ቃሊቲ፤ ከቂሊንጦ እስከ ዝዋይ ያለውን ስቃይ በሚገባ አውቃለሁ፡፡
በአጠቃላይ የአገዛዝ ስርዓቱ የፈለገውን
ሊያደርገኝ
እንደሚችል
አውቃለሁ፡፡
ግን
አልፈራሁም፡፡
ወደፊትም አልፈራም፡፡ ምክኒያቱም
ያለነፃነት
እና ሰብዓዊ ክብር መኖር ከነዚህ
ሁሉ
በላይ
ያስፈራኛል፡፡
ያለነፃነት ለመኖር ሳልፈራ ለነፃነት በነፃነት መሰቃየትንና መሞት
አልፈራም፡፡ እኔ ልፈራ
የሚገባኝ ሕይወቴን
ያለክብር እንዳልመራ
ነዉ እንጂ
ክብር የተነፈገዉ
ሕይወቴን እንዳላጣ
አይደለም፡፡
ከዚህ ሁሉ ስቃይ ጀርባ ነፃነት አለ፡፡ ከዚህ ሁሉ ስቃይ በላይ ሃገር አለች፡፡ ከሃገርም በላይ ስለሃገራዊ ክብሩ የሚሞት ከአፈሩ ጋር በደም
የተቋጠረ እና እትብቱን የቀበረ ህዝብ አለ፡፡ ከሰላማዊ ታጋዮች ስቃይ እና ሞት ጀርባ የእልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ብሩህ የነፃነት
ኑሮ አለ፡፡
ፖሊስ፣ ደህንነት እና ወታደሩ ሲያሰቃየኝ ‹‹ግን ለምን?›› ብዬም እራሴን እጠይቃለሁ፡፡
ከእነርሱ በትርና ከእኛ ስቃይ ጀርባ ያሉትን የሃገሬን የነገ ተስፋ ህፃናት ልጆቹን አስባለሁ፡፡ ከዚህ ሁሉ ስቃይ ጀርባ በልቶ የሚያድር
ቤተሰብን እና እየሳቁ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕፃናት ልጆቹን እመለከታለሁ፡፡ ከዚያም እራሴም እመልሳለሁ፡፡ በአንድ እኔ ስቃይ ስንት
ህፃናት ዳቦ በልተው አድረው ይሆን? የእኔ ስቃይ ለስንት የወታደር፣ የደህንነት እና የፖሊስ ህፃናት ልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ
መሆን ችሎ ይሆን? ይህ ነው የዘወትር ጭንቀቴ፡፡ ስለዚህም ፖሊስ፣ ደህንነት እና ወታደሩ የትግል አጋሬ ነው፡፡ አንድ እኔን አሳቃይቶ
እልፍ እኔዎችን ይፈጥራል፡፡ አንድ እኔን ገድሎ እልፍ እኔዎችን ያኖራል፡፡
ነገ ግን በእኔ ስቃይ እና ሞት የኖሩ እነዚህ እልፍ እኔዎች አደባባይን ያጥለቀለቁ
ቀን ተኩሶ የሚገላቸው እና አስሮ የሚያሰቃያቸው ይጠፋል፡፡ ያኔ ለአምባገነኖች እንደ ጀግናው ባሻ አውአሎም ሀረጎት ‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና›› ብያለሁ፡፡
በአድዋ ጦርነት ወቅት ነው አሉ፡፡ ጦሩን እየመገቡ ማቆየት ለነ ምኒልክ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። በአስቸኳይ
ጦርነቱ ካልተጀመረ በምኒልክ በኩል ችግር ሊፈጠር ሆነ። ጣሊያን ያለበት ሄደው እንዳይወጉት ቦታው አመች አልነበረም። ተመካከሩ።
ወሰኑ። ባሻ አውአሎም ሀረጎት ተጠርተው ተነገራቸው። ጀግናው ተስማሙ። ወደ ጣሊያን ሠፈር ሄዱ። ንገሩ የተባሉትን በኢትዮጵያ በኩል
ስንቅ ማለቁንና በሽታ መግባቱን ለጄነራል ባራቴሪ ነገሩት። እጅግ በጣም ተደሰተ። የካቲት 23 ቀን አድዋ ደረሰ። ባሻ አውአሎም
ሀረጎት የአሉላ አባነጋን ጦር ሲመለከቱ ሮጠው ወደ እነ አሉላ ምሽግ ውስጥ ገቡ። ባራቴሪ ‹‹አውአሎም…አውአሎም…አውአሎም›› ብሎ
ሲጠራቸው ‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና›› አሉት። ውሎህን አያውለኝ ማለታቸው ነው።
ህዝብ እስከ አሁን የተሸከመው ባርነት እና ጭቆና ከዚህ በኋላ የዚህኑ ያክል ይሸከማል ማለት አይደለም፡፡
ሺህ የዋጋ ጭማሪን የተቀበለ ህዝብ ሰባራ ሳንቲምን መሸከም ያቅተዋል፡፡ ያንን መቋቋም ሲሳነው እምቢኝ ብሎ አደባባይ የወጣን ህዝብ
ስርዓቱን በማይነሳበት ደረጃ ሳይቀብር አይመለስም፡፡ ለዚህም በቂ የታሪክ ምስክር አለኝ፡፡ ንጉሱ የጫኑበትን የባርነት እና የጭቆና
ቀንበር ተሸክሞ በጭሰኝነት ለዘመናት የኖረው ሃገሬ ንጉሱን ለመጣል የአስር ሳንቲም የነዳጅ ጭማሪ ምክኒያት ሆነች፡፡ በመቶ እና
በሺህ አሜን ብሎ ሲዘረፍ የኖረው ዜጋ አስር ሳንቲምን መታገስ አቃተው፡፡
አፈር በልቶና ደም ተፍቶ ያረሰውን የሚያስረክበው ገበሬ፣ በእጥፍ እጥፍ ለሚጨምር የኑሮ ውድነት የተዳረገው
ከተሜ እንዲሁም በሚሊዮኖች በባለስልጣናት የሚቀማው ባለሃብት የአስር ሳንቲምን ጭማሪን መቋቋም ይሳነዋል፡፡ ያንገበግበዋል፤ ይጎፈንነዋል፡፡
ቀኑ ሲደርስ አምባ ሲፈርስ መሸሸጊያ ጥግ ይጠፋል፡፡ እንደ ቅዱስ ቃሉ ‹‹ብቻዬን ነኝ ፈራሁ እሸሸግበት ጥግ አጣሁ›› ያስብላል፡፡
የዛን ቀን የአምባገነኖችን ውሎ አያውላችሁ፡፡ ‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና›› ማለት ያኔ ነው፡፡
በአስር ሳንቲም የዋጋ ጭማሪን ተቃውሞ አደባባይ የወጣን ህዝብ እንኳ በቅናሽ በነፃ እደላም ወደ ቤቱ
አይመለስም፡፡ ያኔ ከአደባባዩ የመንግስት ጥይት፣ የቀን ሃሩር፣ የሌሊት ቁር አሊያም ደግሞ ረሃብ እና ቸነፈር ህዝቡን ወደ ቤቱ
አይመልሰውም፡፡ በቤቱ እና በአደባባዩ መካከል ያለው ልዩነት ይጠፋል፡፡ ምክኒያቱም እዛም ቁር እና ሃሩር አለ፡፡ እዛም ረሃብ እና
ቸነፈር አለ፡፡ እዛም የማይቀረው ሞት አለ፡፡ ያኔ የመንግስት እንገድላለን እና እናስራለን ዛቻ ፈርቶ ወደ ቤቱ የሚመለስ አይኖርም፡፡
ያ ቀን ሲደር ለአምባገነኖች የግድያ እና እስራት ዛቻ የህዝቡ ምላሽ ‹‹ገላገላችሁኝ›› ይሆናል፡፡ ምክኒያቱም በሞት እና በህይወት
እንዲሁም በመታሰር እና አለመታሰር መካከል ያለው ልዩነት ይጠፋል፡፡ ያኔ ህዝብ ምንም ነገር አይፈራም፡፡
የቁርጡ ቀን ሲደርስ ገበሬው ማረሱን ያቆማል፡፡ በሬዎች ይለግማሉ፡፡ የዛን ቀን ለሞፈር እና ቀንበር
እንጨት የሚቆርጥ ይጠፋል፡፡ በገበሬው አለማረስ ምክኒያት በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይከሰታል፡፡ መምህሩ ማስተማሩን
ተማሪዎች መማርን ያቆማሉ፡፡ ፋብሪካዎች ይዘጋሉ፡፡ ያኔ መንግስት ተብዬውን አያድርገኝ፡፡ የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪውን ይበላል
የሚለው የፖለቲካ መርህ ተግባር ላይ ይውሏል፡፡ ‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና›› ማለት ታዲያ ያን ጊዜ ነው፡፡
መቼ ብላችሁ እንዳትጠይቁኝ፡፡ ትክክለኛ ቀኑን ባላውቅም በቅርብ እንደሆነ ግን በሚገባ አውቃለሁ፡፡
የህዝባዊው ቁጣ ቀን ሽታ ወደ አፍንጫዬ ሲደርስ ምን ያክል ቅርብ እንደሆነ ያሳውቀኛል፡፡
ሃገሬን አለቅም!!!
ቸር ያገናኘን!!!
No comments:
Post a Comment