Monday, 25 August 2014

ሲሞት ምን ተሰማ?



ንጋት ላይ ነበር አባቴ ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ፡፡ ፍጹም ፊቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ድንገጤ ይንበብ ነበር፡፡ በወቅቱ ከእንቅልፌ ገና በድንብ ስላልነቃሁ የአባቴ ድንጋጤ እና ሃዘን ፍጹም እኔንም አስደንግጦኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የተናግረው አረፍተ ነገር ግን ፍጹም ድንጋጥዬ ለራሴም እስኪያስደነግጠኝ ድረስ ነበር የደነገጥኩት፡፡ "ምን?" አልኩት፡፡ "መለስ ሞተ"ደገመው፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡
መብራት ጠፍቶ ስለነበር ሚዲያ መከታተል አልቻልንም ነበር፡፡ የሞባይሌን ሬድዮ ከፈትኩ ሃዘን ያደቀቀው የጋዜጠኞች ድምጽ እና የክላሲካል ሙዚቃ እየተፈራረቀ ይሰማል፡፡ በመጨረሻ ተረጋግቼ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ አንድ እና አንድ ጥያቄ እራሴን ጠየኩ፡፡ ለምን? ለምን የዚህን ያህል ደነገጥኩ? ይህ የአገዛዝ ስርዓት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ እልፎች በጥይት እና በረሃብ ሲያልቁ በአይኔ አይቻለሁ እንዲሁም በጆሮዬ ሰምቻለሁ፡፡ ግን ዛሬ ይህንን ሁሉ የሚፈጽመው እና ህዝቡን የሚያሰቃየው ቡድን መሪ ሲሞት ከዚህ በፊት ከሰማሁት አሰቃቂ ነገሮች በላይ አስደነገጠኝ፡፡ በወቅቱ ግን "ለምን የዚህን ያህል ደነገጥኩ?" ለሚለው ጥያቄዬ በቂ ምላሽ አላገኘሁም ነበር፡፡
ከቀኑ ወደ 4፡00 ሰዓት ገደማ አንድ የኢህአዴግ አባል የሆነ ወዳጄ እንዳገኘኝ ከሰላምታ አስቀድሞ "ምን ተሰማህ?" አለኝ፡፡ በወቅቱ የሀዘኑ ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ ባልችልም ሃዘኑ ከውስጤ ስላልወጣ እጅግ በጣም ማዘኔን ገለጽኩለት፡፡ እርሱ ግን ወዲያው አንድ ነገር ተናገረ "ጥላቻክ መሰረት አልነበረውም፡፡ ዝም ብሎ ጭፍን ጥላቻ ብቻ ነበር፡፡ ለነገሩ ሰው ካልሄደ እና ካልሞተ አይመሰገንም" ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡
"እውነት ግን ጥላቻዬ ምክንያት አልነበረውም?" ብዬ እራሴን ጠየኩት፡፡
ውስጤ ግን ዝም ስልክ አበዛከው ብሎ ነው መሰል ያለችግር መልሱን ያምበለብለው ጀመር፡፡
"ምክንያትማ ነበረህ" ብሎ ጀመረ፡፡ ቀጥሎም "ስንቶች በርሱ የስልጣን ዘመን ብቻ ሳይሆን በርሱ ትዛዝ በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ አላየህም? አልሰማህም? ሚሊዮኖች በርሱ የተሳሳተ ፖሊሲ በጦርነት እና በረሃብ ሲልቁስ አልተመለከትክም? በብዙ ሸህ የሚቆጠሩ ወንድም እና እህቶችህ በደሃ ሀገር እና በደሃ ቤተሰብ ገንዘብ ተምረው በስራ ማጣት ሲቸገሩስ በአይንህ በብረቱ አላየህም? የተማረ የሰው ኃይል እጥረት አለብን በሚል ሰበብ ወረቀት እንጂ እውቀት የሌለው የውጪ ዜጋ በብዙ ሺህ ዶላሮች ሲዝቅ አይተው ከርሱ የተሻለ እውቀት ከወረቀት አጣምረው የያዙ የሀገርህስ ምሁሮች አገር ጥለው ሲሰደዱስ የት ነበርክ? ሺዎች በኮንቴነር፣ በእግር እና በባህር እያቆራረጡ ወደ አውሮፓ እና አፍሪካ ለመሰደድ ሲሞክሩ እና ህይወታቸው ሲያልፍ በስልጣን ላይ የነበረው ማን መሰለክ? ይሄው እርሱ አልነበረም እንዴ? እልፎችን ለምን እንዲህ አላችሁ፣ ለምን እንዲህ ጻፋችሁ፣ ለምን እንዲህ አደረጋችሁ እያለ በየ እስር ቤቱ ሲያጉራቸው የነበረውስ እርሱ አልነበረም እንዴ? ሌላው ቢቀር ስንት ዘመናት ደም ፈሶ እና አጥንት ተከስክሶ ተከብሮ የኖረውን እና የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን ባንዲራ ጨርቅ ብሎ በአደባባይ የሰደበው ብሎም ዛሬ በየትምህርት ተቋማቱ ተማሪዎች ጎራ ለይተው ይጣሉበት ዘንድ ብሔር የሚለውን የአንድነት መሰረት የልዩነት መሰረት ያደረው ማን መሰለህ ይሄው ዛሬ ምንም እንዳላደረገ ሰው የሞተው አይደለም?" ብሎ በጥያቄ ሲያፋጥጠኝ መቆም ተስኖኝ ነው መሰለኝ ከሃሳቤ የአስተናጋጅዋ የምን ልታዘዝ ጥያቄ ሲያነቃኝ ከአንድ ካፌ ቁጭ ብዬ እራሴን አገኘሁት፡፡ ታዲያ ለምን ነበር ሞቱን ስሰማ እንዲያ የደነገጥኩት እና ያዘንኩት? መልሱ አሁን ቀላል ሆነልኝ፡፡
አንድ ህልም ነበረኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በእርሳቸው እና በግብረ-አበሮቻቸው ሲደርስበት የነበረውን አስተዳደራዊ በደል ተወግዶ፣ በሃገሪቷ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መተዳደር ጀምራ፣ ብሔራዊ እርቅ ወርዶ እንዲሁም ህዝቦች በዘር እና በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ቀርቶ ሁሉም ለአንድ አላማ ያለምንም ልዩነት በአንድነት በድህነት ላይ የሚዘምቱበት ጊዜ መጥቶ በቁማቸው እንዲያዩ እመኝ ነበር፡፡ ይህንንም ብቻ አይደለም የሚጠሉትን ይቅርታ የመጠየቅ ጉዳይ በአደባባይ ስራቸው ስህተት መሆኑን አምነው ህዝብን ይቅርታ ሲጠይቁም መስማትም እፈልግ ነበር፡፡
ሕዝብን የሚያሰቃይ እና በህዝብ ስቃይ የሚዝናና እና ሃብት የሚያካብት የአምባገነን ስርዐት አራማጆችን ከማሰር ወይም ከመግደል ይልቅ እራሳቸውም ሆነ ሌሎች ላይ ምንም እንዳያደርጉ አደርጎ የማይፈልጉትን በጎ ነገር እንዲያዩ እና እንዲሰሙ ማድረግ ከቅጣትም በላይ ነው፡፡ ሰይጣንን የለመደው ገሃነም አስገብቶ ከመቅጣት እራሱም ሆነ ሌሎች ላይ ምንም እንዳያደርግ አደርጎ የበጎ ነገሮች መገኛ ከሆነው ገነት ማስቀመጥ ትልቁ እና ሊቋቋመው የማይችለው ቅጣት ነው፡፡ መልካም ላላደረገ ሰው መልካም ማድረግ ከቅጣትም በላይ የሆነ ቅጣት ነው፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ህልሜም እውን ከመሆኑ በፊት ግን የስርዓቱ አውራን ሞት ቀደማቸው፡፡ አሁንም ለተቀሩት ይህንኑ እመኛለው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ያበደራቸው እና ያልከፈሉት ብድር አለ፡፡ አዎ በጫካ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ-መንግስትን እስኪረግጡ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ እየተቀባበለ ከሚበላው እና ከሚለብሰው እየቀነሰ ሲቸራቸው ይህም ብቻ ሳይሆን በየጭድ ክምሩ፣ በየ አልጋው ስር እና በየኮርኒሱ ውስጥ ሸሽጎ ከብሔራዊ ውትድርና ጣጣ ያቆየውን ልጁን ወታደር ይሆናቸው ዘንድ ሲሰጣቸው ዋናው አላማ ያደረገው ነገ ከሰጠኋቸው የተሻለ ይሰጡኛል ብሎ እንጂ ዘመናዊ አምባገነንነት ያሳዩኛል ብሎ አልነበረም፡፡
ለአምባገነንነቱማ ማን እንደ ደርግ ነበር፡፡ ደርግ እኮ መስራትም መግደልም በደንብ አድርጎ ያውቅበት ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የነበረው በአደባባይም ይሁን በሚስጥር መግደሉን ትቶ በአግባቡ ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት እንዲሁም ሃገሪቷን ወደ ነበረችበት ሃያልነት ለመመለስ የሚሰራ እና የሚያሰራ መሪ ነበር፡፡
እነሆ እርሳቸው ቤተ-መንግስቱን ከረገጡ እንዲሁም ግብረ-አበሮቻቸውም ወንበራቸውን ከያዙ ሁለት አስርት አመት ያለፋቸው ቢሆንም እንኳ ከደርግ የተለየ ያደረጉት ነገር እንብዛም የለም፡፡ ደርግ ስርአቱን የተቃወሙትን ያስራል፣ ያሰቃያል ብሎም ይገድላል እንዲሁም ወጣቱን በየጦርነቱ ይማግዳል፡፡ አሁንስ ይሄ መች ቀረ፡፡ አሁንም ስርዓቱን መቃወም ያሳስራልም ያስገድላልም፡፡ ወጣቱም በየጦር ግንባሩ ይማገዳል፡፡ ግን ይህ ሁሉ ሲደረግ ደርግ ሲያደርግ እንደነበረው ስርኣቱን መቃወም በቀጥታ አያሳስርም ወይም አያስገድልም፡፡ ወጣቱም ከቤተሰቡ ጉያ እየተነጠቀ ወደ ጦርነት አይማገድም፡፡
ሁሉም ነገር ህግ እና ስርዓት ይበጅለታል፡፡ በህግ እና ስርዓት ምክንያት ተፈልጎ ይታሰራል ብሎም ይገደላል፡፡ ጦርነት ሲታሰብም ወጣቱ በስራ አጥነት እንዲሰቃይ ይደረጋል ከዚያም ውትድርና እንደ ብቸኛ አማራጭ ይቀርብለትና እንዲመርጥ ይደረጋል፡፡ መቼም በርሃብ ከመሞት በጥይት መሞት ሳይሻል የሚቀር አይመስለኝም፡፡ መቼም እንደ ውትድርና የውስጥ ፍላጎት እና ተነሳሽነት የሚፈልግ የተከበረ ሙያ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ውትድርና የምርጫ ማጣት ጉዳይ ሳይሆን ህዝቦችን እና ሃገርን ከአደጋ የመጠበቅ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ጉዳይ ነው፡፡
ይህንን ሃሳብ ሳወጣና ሳወርድ ቆይቼ የነበርኩበትን ካፌ ለቅቄ ወደ መኖሪያ ቤት አመራሁ፡፡ ቀኑን ሙሉ የቴሌቨዥን እና የሬድዮ አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያስታውሱ ታሪኮችን ሲነግረን ነበር የዋለው፡፡
በማግስቱ ወደ ኢንተርኔት ማዕከል አመራሁ፡፡ ኢንተርኔት ማዕከል እንደደረስኩ የፌስቡክ እና የኢ-ሜይል አካውንቴን ነበር የከፈትኩት፡፡ የተለያዩ ሰዎች የመለስን መሞት አስመልክቶ የሃዘን እና የደስታ መግለጫ መልዕክት ትተውልኝ ነበር፡፡ ጀግና አይሞትም፣ መለስ አልሞተም፣ ሞት ብርቃችን አይደለም፣ እንኳን መለስ የሰፈራችን ጉልቤም ሞቷል፣ ድብን ይበል፣ ሲያንሰው ነው እና የመሳሰሉት ከተላኩልኝ መልክቶች ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን "መለስ አልሞተም አለ" በሚል አርዕሰት የመንግስት ሚዲያ ለለቀቀው ግጥም የመልስ ምት ይሆናል ተብሎ የተለቀቀው ግጥም ቀልቤን ስቦት ነበር፡፡ እንዲህ ነበር የሚለው፡-
መለስ አልሞተም አለ
በአመለካከት መታሰር÷ በዘር መገፋት ካልቀረ፤
በአድር ባይነት ቁራኛ÷ የዘርኛነት ደዌ ካልሻረ፤
የይስሙላ ፍርድ ቤት÷ የግብር ይውጣ ምርጫ፤
የአንድ ብሔር ፖለቲካ÷ የአንድ ግለሰብ ብልጫ፤
የእስክንድር ነጋ እሮሮ÷ የርዕዮት አለሙ ጩኸት፤
የአንዱአለም አራጌ ሰቆቃ÷ የብዙሃን ልጆችሽ ስደት፤
ይህ ሁሉ አሳር መከራ÷ ነገም እንዳለ ካለ፤
እውነትም ልክ ብላችኋል÷ መለስ አልሞተም አለ፡፡
ሸጋ ግጥም ነው፡፡ የግጥሙን ባለቤት አመስግኛለሁ፡፡ የግጥሙ ባለቤት የዘረዘራቸው እነዚህ ሁሉ የመለስ ቋሚ ሃውልቶች ናቸው፡፡ መለስ ሞተ ለማለት እነዚህ ሁሉ መወገድ እና መሞት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ወዳጅ ዘመዶቹ እንዳሉት መለስ አልሞተም፡፡
በመጨረሻም እኛ ኢትዮጵያውያን ከድህነት በስተቀር ለማንም ሞትን አንመኝም፡፡ ጠላቶቻችንን የመበቀል ባህል የሌለን ህዝቦች ነን፡፡ ስላሰሩን፣ ስላሰቃዩን፣ ስለወጉን እና ስለገደሉን ተመሳሳይ ነገር እነርሱን ለማድረግ አንመኝም፡፡ የኛ ምኞት ለአገዛዝ ይመች ዘንድ በመካከላችን ያስቀመጣችሁትን የመጠላላት ስሜት ማስወገድ እና ብሔራዊ እርቅ ማውረድ ነው፡፡ ሁላችንም ፈር ከለቀቀ ጎሰኝነት እና ጎጠኝነት ወይም መንደርተኝነት ስሜት መላቀቅ አለብን፡፡ ከልዩነታችን በላይ አንድነታችን እንዲሁም ከጎሰኝነት በላይ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ መታየት ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሁላችንም የምናደርገው ጌጣችን ሲሆን ጎሳዎቻችን ደግሞ የጌጣችን ፈርጦች ናቸው፡፡ ጌጡ ያለፈርጥ አያምርም፤ ፈርጡ ግን ያለጌጡ የለም፡፡ ልዩነታችን፣ መከፋፈላችን እና መጠላላታችን ለጠላት እንጂ ለወዳጅ አይበጅም፡፡ ለጠላት አንመች፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ይህንን አንድነታችንን ሲያዩ አይናቸው ደም ይለብሳል፡፡ ምክንያቱም አንድነታችን ያጠነክረናል፤ ጥንካሬያችን ደግሞ እነርሱን ያስፈራቸዋል፤ ፍራቻቸው ደግሞ ያዳክማቸዋል፤ በመጨረሻም ድካማቸው ያጠፋቸዋል፡፡ ስለዚህ አንድነታችን ስለሚያጠፋቸው አንድነት እንዲኖረን አይፈልጉም፡፡ ጉዳዩ ግን አንድነታችን የእነርሱ መፈለግ እና አለመፈለግ ሳይሆን የእኛ ፍላጎትን ብቻ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡
አምባገነኖች በአምባገነን ስርዓት ለማስተዳደር የሚያስፈልጋቸው ዋናው ነገር የሚመሩት ህዝብ ፍቃደኝነት ነው፡፡ ገጣሚው ዮቭጊነይ እንዳለው ለህገ-ወጥ ስርዓት መስፋፋትና ለፍትህ መጓደል ተጠያቂዎቹ የአገዛዙ ስርዓት አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆኑ እነርሱ የፈለጉትን እንዲያደርጉ የፈቀደላቸው ህዝብም ጭምር ነው፡፡
ነገ አዲስ ቀን ነው፡፡ ማን ያውቃል? አዲስ ታሪክ ይዞ ሊመጣ ይችላል!!
የነገ ሰው ይበለን!!


No comments:

Post a Comment