Sunday, 15 June 2014

የግንቦት 20 ጫፍ አልባ ቁልቁለቶች




የግንቦት 20 ጫፍ አልባ ቁልቁለቶች-1

መግቢያ
ተጋዳላዮቹሰ ነፍጥ አንግተው ‹‹ብሶት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት ወታደራዊ ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል፡፡ ግንቦት 20, 1983›› ብለው አውጀው ሃገሪቷን ከተቆጣጠሩ በኋላ የግንቦት ፀሃይ ቡዳ በልቷቸው ነው መሰለኝ ከአመት አመት እንደ ግንቦት ፀሃይ እያቃጠሉን እንደዋዛ 23 አመታት አልፈዋል፡፡
በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ከዚህ በታች ድህነት የለም ብለን ነበር፡፡ በዚህ ስርዓት-አልባ ስርዓት ከድህነትም ወጥተን የድህነት አዘቅትም እንዳለ አሳይቶናል፡፡ በወታደራዊ ደርግ ዘመን የጭቆና እና አፈና መጨረሻ አይተናል ብለንም ነበር፡፡ የባሰም አለና ሃገርህን አትልቀቅ እንዳለው ሃገሬ በዲሞን-ክራቱ ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ ለባርነትም ሆነ ለጭቆና ከእኔ በላይ ላሳር ያለን አገዛዝ ለማየት በቅተናል፡፡
በዚህ ፅሑፍ ስር ደርግ ቁ-1 በሚገባ ተጠናቆ ደርግ ቁ-2 ልዩ ስሙ ኢህአዴግ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ባለፉት 23 አመታት ውስጥ ሃገሪቷ እንደ ናዳ ቁልቁል የተንከባለለችባቸውን እንዳንድ ዘርፎች እያነሳን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ከእነዚህም ዋነኞቹ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች መፈልፈያ ማዕከል የሆኑት የትምህርት ተቋማት፣ እንደሸንበቆ እያደገ ነው የተባለለትና የህዝቦችን የመኖር ህልውና እንደሙቀጫ ቁልቁል ያንከባለለው የኢኮኖሚ ስርዓት፣ የባለስልጣናት መፈንጫ የሆነው ፍትሕ አልባ የፍትህ ስርዓት፣ በባለስልጣናት የበላይነት የሚመራውን የህግ የበላይነት፣ ከሃገሪቷ ከ80% በላይ ህዝብን ያሳተፈውና እራሱን እንኳ መመገብ ያልቻለው የግብርናው ስርዓት እና የመሳሰሉትን በዚህ አምድ ስር በተከታታይ በሚወጡ ፅሑፎች ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

ትምህርት እና ግንቦት 20
ይህ ቁልቁለት እውቅ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን የምን እውቀት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ (የጎሳ ተኮር ፖለቲካ እውቀት ሊሆን ይችላል) የ‹‹እውቀት ማነስ›› በሚል ሰንካል (እጅ እግር አልባ) ምክኒያት ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማባረር ተጀምሯል፡፡
ሃገር ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ያስተማረቻቸውን ጉምቱ ምሁራንን ከትምህርት ገበታቸው ላይ በማባረር ከሳይንሱ በላይ ዘረኝነትን በሚሰብኩ የጎጥ ፖለቲካ አቀንቃኝ ምሁራን በመተካት (የመተካካቱ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል) የጀመረው ቁልቁለት ሀገሪቷ ዳግም ልታንሰራራ በማትችልበት የትምህርት ጥራት ችግር ውስጥ ከቷት መገኛውን ኮብልስቶን ስር ካደረገው ምሁር ላይ በማድረግ እነሆ 23 አመቱን ሻማ በማብራት እያከበረ ነው፡፡
የትምህርት ጥራት የአንድን ሃገር መፃኢ እጣ ፈንታ ለመተንበይ ከሚያስችሉ መንገዶች ዋነኛው ነው፡፡ የወያኔ መንግስት ስልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላ ሃገሪቷ በትምህርቱ ዘርፍ ትኩረቷን ከጥራት ወደ ብዛት በማሸጋገር (የትራንስፎረሜሽኑ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል) ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ እየተገበረ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቷ ውስጥ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ጥራት ተኮር ባለመሆኑ በዚህ ፖሊሲ ተወዳዳሪ የሆኑ ሙያተኞችን መፍጠር አልተቻለም፡፡ በቂ እውቀት የሌለው ወጣት ማምረት ደግሞ ስርዓቱን የሚሞግት ትውልድ እንዳይፈጠር በማድረግ የስርዓቱን ቀጣይነት በማረጋገጡ ላይ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማትን ማጥፋት እና ማኮላሸት ዋነኛ እና ቀዳሚ የወያኔዎቹ ስራ የሆነበትም ዋነኛው ምክኒያት ያለፉት መንግስታት የነበራቸው ጥራቱን የጠበቀ እና ነፃ የትምህርት ፖሊሲ በተደጋጋሚ የሚሞግታቸውን ትውልድ በመፍጠር ስልጣናቸውን እንዲያጡ ያደረገው የህዝባዊ ማዕበሉ መነሻ ሆነው ያገለገሉት እነዚህ የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ የትምህርት ተቋማት የለውጥ ሃዋሪያዎች መፍለቂያ ማዕከላት በመሆን ለዘመናት ሃገሪቷን ማገልገላቸው የነፍጠኞቹ ወያኔዎች ማነጣጠሪያ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ እነርሱም ለውጡን የዶለቱት እነዚሁ ማዕከላት ውስጥ መሆኑንም መርሳት አያስፈልግም፡፡
ነፍጠኞቹ (ነፍጥ አንጋቾቹ)፣ ጎሰኞቹ እና ጎጠኞቹ የቀየሱት የትምህርት ፖሊሲ በሚገባ ተግባራዊ በመደረጉ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት ባይ፣ ምክኒያት አልባ፣ መብት እና ክብሩን የሚለምን ትውልድ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የሚገኙ ወጣቶችም በሃገራዊ አንድነት ላይ ከመወያየት ይልቅ አምባገነኑ መንግስት ባቀረበላቸው የጎሰኝነት ድንጋይ መወራወርን ቀዳሚ ተግባራቸው ካደረጉ ሰንበትበት ብለዋል፡፡
ይህንን ስርዓት-አልባ ስርዓት ለማስወገድ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጪ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በትምህርት ፖሊሲዎቻቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ተገቢ እና ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ፖሊሲ ማለት ትውልድ የሚቀረፅበት እንዲሁም የሃገር የወደፊት እጣፈንታ የሚወሰንበት ፖሊሲ በመሆኑ የሁሉም ፖሊሲዎች የጀርባ አጥንት ማለት ይቻላል፡፡
የአንድ ስርዓት ዲሞክራሲያዊነት ማሳያ የትምህርት ስርዓቱ ከፖለቲካ ስርዓቱ ያለው ነፃነት ነው፡፡ የትምህርት ስርዓቱ የፖለቲካ ስርዓቱ አቀንቃኝ ከሆነ ወይም የፖለቲካ ስርዓቱ በከፈተለት ቦይ ብቻ የሚፈስ ከሆነ በሃገሪቷ ያለውን የትምህርት ስርዓት ብልሹነት ማሳያ ነው፡፡ 
በየትምህርት ተቋማቱ በማስተማር እና በመማር ላይ የሚገኙ ምሁራን እና ተማሪዎች ያለምንም ገደብ እና ፍራቻ ሃሳባቸው በነፃነት የመግለጽ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ መምህራን እና ተማሪዎች በፍርሃት እየማቀቁ የሚያስተምሩበት እና የሚማሩበት ይህ የአገዛዝ ስርዓት ሊያበቃ ይገባል፡፡
የትምህርት ስርዓቱ ከፖለቲካው ስርዓት ነፃ ባለመሆኑ መምህራን እንደ ገቢ ምንጭ ብቻ የሚጠቀሙበትን ስራ ላለማጣት ተማሪዎችን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እያገናዘቡ ማስተማር ህልም ይሆንባቸዋል፡፡ የመምህራንን ፍራቻ ለማሳየት ተማሪዎቻቸው የሚጠይቋቸውን ጥያቄ ‹‹ይህ ፖለቲካ ነው እንለፈው›› እያሉ እውቀታቸውን ብቻ ሳይሆን ፍርሃታቸውን ወደ ተማሪው የሚያስተላልፉ መምህራን መሰብሰቢያ ማዕከላት ወደ ሆኑት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡
በግብርና፣ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በጤና … ዘርፍ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በማስተማር የሚገኙ መምህራን የሃገሪቷን ፖሊሲዎች ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እያመሳከሩ የመንግስትን ፖሊሲዎች የመተቸት እና አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብ መንግስትን ከተሳሳተ ጎዳና የማረቅ ሃገራዊ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ትልቅ ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ስራቸው ላለማጣት እራሳቸውን በፍርሃት አዘቅት ውስጥ ከተው የሚዳክሩ መምህራን መመልከት የእለት ተለት ተግባራችን ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ እነዚህን በፍርሃት ባህር ውስጥ የሚዳክሩ ምሁራንን ከተከናነቡት የፍርሃት ካባ ማላቀቅ ከተቻለ ታላቅ ለውጥ ሃዋርያ ማድረግ ይቻላል፡፡
ሌላኛው የትምህርት ሴክተሩ ቁልቁለት በየትምህርት ተቋሙ የሚቀጠሩ መምህራን በሚቀጠሩበት የሙያ ዘርፍ ካላቸው ችሎታ ይልቅ ያላቸውን የጎሳ ፖለቲካ እውቀት በተለይም ለአገዛዝ ስርዓቱ ያላቸውን ታማኝነት ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ የትምህርት ጥራቱን ቁልቁል በእንብርክክ እንዲሄድ አስገድዶታል፡፡ እነዚህ መምህራን ተብዬዎች ከስርዓቱ ደሞዝ ብቻ ሳይሆን የሚሰፈርላቸው የሚያስተምሩት ወይም የሚያስተላልፉትም እውቀትም ይሰፈርላቸዋል፡፡ እንደገደል ማሚቱ የተባሉትን እና እንዲሉ የተፈቀደላቸውን ብቻ ለተማሪዎቻቸው ያስተጋባሉ ወይም ያስተላልፋሉ፡፡
በመጨረሻም በሃገሪቷ ውስጥ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በማያዳግም ሁኔታ መፍትሔ ለመስጠት በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ ዜጎችን የማፍራት ተግባራቸው ላይ ያለምንምና ማንም ጣልቃ ገብነት ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ የትምህርት ዘርፉ በእውቀት እና በእውነት እንጂ በፖለቲካ ብቃት እና ታማኝነት የሚመራበትን ስርዓት ማስወገድ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ እስካሆነ ድረስ የትምህርት ዘርፉ የሚያመርታቸው ዜጎች ችግር ፈቺ ሳይሆኑ ችግር ፈጣሪ መሆናቸው አይቀርም፡፡  
ስለትምህርት ጥራት ሲባል ይህ ስርዓት አልባ ስርዓት ይፍረስ!!
የሳምንት ሰው ይበለን!!

No comments:

Post a Comment