Monday, 23 June 2014

የግንቦት 20 ጫፍ አልባ ቁልቁለቶች-2

ኢኮኖሚ እንደ ‹‹ሸንበቆ›› ህዝብ እንደ ሙቀጫ

ለመሆኑ መንግስት ስለሚያወራው ኢኮኖሚ ህዝቡ ምን ያክል ገብቶታል? ህዝቡስ ከእድገቱ ምን አተረፈ? ማነው ያደገው? እንዴት ነው ያደገው? የሚሉት እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ዘወትር ወደ ጭንቅላቴ እየመጡ እረፍት ይነሱኛል፡፡ መንግስት እና ህዝብ በቀጥታ ቀርቶ በአስተርጓሚ እንኳ መግባቢያ ቋንቋ ካጡበት ዘርፍ ዋነኛው እንደ ሸንበቆ እያደገ ነው የተባለለት እንዲሁም ሃገራዊ ፍቅርን፣ ህዝባዊ ክብርን፣ ዲሞክራሲን፣ ፍትህን፣ ነፃነትን እና የህዝቦችን የመኖር ህልውን እንደ ሙቀጫ ቁልቁል ያንከባለለውን የኢኮኖሚ ስርዓት በዚህ አጭር ፅሁፍ ለመዳሰስ እሞክራለው፡፡
ህዝብ እና መንግስት አንድ ቋንቋ መናገር አልቻሉም፡፡ የመንግስት ቋንቋ ገብቶናል ያሉት ሃገር በቀል እና የውጪ የመንግስት አፈ ቀላጤዎችም ህዝቡ በሚገባው ቋንቋ መናገር ተስኗቸው ማሳመን (convince) ባይሳካላቸውም ማደራገር (confuse) በጥቂቱም ቢሆን እየተሳካላቸው ይገኛል፡፡

ህዝብ ዘወትር እየተመነጠቀ ስላለው የኑሮ ውድነት ሲያወራ መንግስት ስለ ‹‹ባለሁለት አሃዙ›› እድገት ያወራል፡፡ ህዝብ ስለ ስራ-አጥነት ሲያወራ መንግስት ‹‹ስለኢንቨስትመንት መስፋፋት›› ይደሰኩራል፡፡ ህዝብ ስለረሃብ መንግስት ‹‹ስለጥጋብ››፤ ህዝብ ስለዳቦ መንግስት ‹‹ስለመሰረተ ልማት›› እያወሩ መግባባት ተስኗቸው 23 አመት ያላቻ ጋብቻ በዓላቸውን አንዱ የደስታ ሌላኛው የሃዘን ሻማ በማብራት አክብረው አሳልፈዋል፡፡ ከእንደዚህ አይነት ስርዓት አልባ ስርዓት ጋር ፍቺ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡  

ሃገርን ለመምራት ከተፈለገ ከህዝብ ጋር አንድ ቋንቋ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ቋንቋ ሲባል አማርኛ፣ ኦሮምኛ ወይ ትግርኛ አለያም ወላይትኛ ወይም አፋርኛ ወይ ደግሞ ሱማልኛ … ወ.ዘ.ተ ማለት ሳይሆን ህዝብ የሚለውን መንግስት መስማት አለበት፡፡ መሪነት ከህዝብ ጋር መግባባት ማለት ነው፡፡ ከህዝብ ጋር መግባባት ሳይኖር ሲቀር ገዢነት ይፈጠራል፡፡ አሁን ያለው ስርዓት አምባገነን የገዢነት ስርዓት ነው የሚባለውም ህዝብ የሚለውን መንግስት መስማት ስለተሳነው እና የህዝብን ጥያቄ በተቃራኒው በመመለሱ ማለትም ህዝብ ኑሮ ተወደደብኝ ወይም ራበኝ ሲል የመንግስት መልስ ገበሬውን ከእርሻው በማፈናቀል፣ የማዳበሪያ እና የዘር ዋጋን በማናር ገበሬው እንዳያመርት ወይም ያመረተውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይሸጥ በማድረግ ገቢያውን ከማረጋጋት ይልቅ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ማስገባቱ ነው፡፡

በአንድ ሃገር የምጣኔ ሃብት (የኢኮኖሚ) እድገት አለ ለማለት በትንሹ የህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎት ተሟልቶ በሃገራቸው የመኖር ዋስትናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የምጣኔ ሃብት እድገት እና የህዝቦች የመኖር ህልውና በቀጥተኛ መንገድ የተያያዙ ናቸው፡፡ በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ነው ማለት የህዝቦች በሃገራቸው የመኖር ህልውናቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ መሬት ላይ ያለው እውነታ (facts on the ground) ይህንን ይነግረናል?


በሃገሪቷ ውስጥ ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት አለ ለማለት ህዝቦች ቢያንስ ያለ ምንም ልዩነት መሰረታዊ ፍላጎቶች ተብለው የሚጠሩትን ማለትም ምግብ፣ አልባሳት እና መጠለያ ለማግኘት የሚጓዙት መንገድ ምን ያክል ከትላንት ዛሬ እንዳጠረ ብቻ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ለስርዓት አልባው ስርዓት ቅርብ ወይም የገዢው መደብ አባላት ካልሆኑ በስተቀር ዛሬ ላይ ቆመን እነዚህ ነገሮች የማያስጨንቁት የህብረተሰብ አካል አለ ብሎ ለማሰብ በማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡
የልጆች ምግብ እና አልባሳት የማያስጨንቀው ቤተሰብ ወይም አሳዳጊ እንዲሁም የመጠለያ ችግር የማያማርረው ዜጋ ማግኘት ከጭድ ክምር ውስጥ መርፌ የማግኘት ያህል ከባድ ከሆነብን እነሆ ሁለት አስርት አመታትን አሳልፈናል፡፡ ታዲያ ከገዢው መደብ አባላት ውጪ የህዝቦችን መሰረታዊ ፍላጎት በትንሹ እንኳ ማሟላት ያልቻለው የምጣኔ ሃብት እድገት ምን ማለት ነው?

በአንድ ሃገር ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት በባለስልጣናት ኪስ ወይም በድንጋይ ቁልል ወይም ንጣፍ መለካት ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለአምስት አመታት ስትገዛ የባንዳዎችን (የባለስልጣናትን) ኪስ አደልባለች እንዲሁም አሁንም ድረስ ለምስክርነት የቆሙ መንገዶችን ህንፃዎችን ገንብታለች ነገር ግን ህዝቦች በሃገራቸው በነፃነትና በሰላም የመኖር መብታቸውን ነፍጋለች፡፡ ጣሊያን የነፈገቻቸው የህዝቦች በሃራቸው እንደ ሰው በሰላም እና በነፃነት የመኖር መብታቸው ከሰራቻቸው የመሰረተ ልማት መስፋፋት ጋር ማወዳደር ለማንም ኢትዮጵያዊ የማይዋጥ ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ስርዓት ከዚህ የተለየ ምን አደረገ?

በአንድ ሃገር ያለ የምጣኔ ሃብት እድገት መለካት ያለበት በህዝብ የኑሮ መሻሻል ነው፡፡ የህዝቦች በሃገራቸው በክብር፣ በሰላም እና በነፃነት የመኖር ዋስትናቸው በምን ያክል ተረጋግጧል?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ዜጎች በሃገራቸው ሰርተው መሰረታዊ ፍላጎታቸው ማሟላት ተስኗቸው ብሎም በአያት በቅድመ አያታቸው መሬት በሰላም፣ በክብር እና በነፃነት መኖር አቅቷቸው ስንቶች በታንኳ ባህርን አቋርጠው፣ እንደ ጨርቅ በኮንቴነር ታሽገው እንዲሁም በረሃን በእግር ጉዞ አቋርጠው የባዕድ አገር ለመግባት እየሞከሩ በየመንገዱ ወድቀው የበረሃ እና የባህር ሲሳይ ሆነው የቀሩትን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ እንዚህ ወገኖቻችን የኢኮኖሚው እድገት የፈጠራቸው የሰላም ተጓዥ ወይም ቱሪስት አይደሉም፡፡ እነዚህ ዜጎች የነገ ተስፋቸው የጨለመባቸው የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግፉዓን ናቸው፡፡

ዛሬ የባዕድ ሃገራትን ያሞቁ ያደመቁት የዚህ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስርዓት ግፉዓን አይደሉምን? ታዲያ ምኑ ጋር ነው የምጣኔ ሃብት እድገት ያለው? ዳቦ ቀርቶ ተስፋ መሆን ያልቻለ የኢኮኖሚ እድገት ባለሁለት ሆነ ባለሶስት አሃዝ ምን ዋጋ አለው?

ቢያንስ የተማረውን ወጣት እንኳ የስራ ባለቤት ማድረግ ያልቻለ የኢኮኖሚ እድገት በየትኛውም መለኪያ ተዓማኒ ሊሆን አይችልም፡፡ የአለማችን ግንባር ቀደም ከሚባሉት የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑት ሃገራት ተርታ ‹‹ቀዳሚ ነን›› እያልን የስራ አጥነቱ ከቀን ወደ ቀን በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ በቀጠለበት ሃገር ውስጥ የሚኖር ህብረተሰብን ለማሳመን መሞከር እራስን ማሞኘት ነው፡፡

ተምሮ እና ተመርቆ ከቤተሰቡ ጫንቃ ላይ መውረድ የተሳነው ወጣት ባለበት ሃገር ስለ ምጣኔ ሃብት እድገት እና ስለኢንቨስትመንት መስፋፋት መለፈፍ ምንኛ መራር ቀልድ ይሆን?

አርሶ እና አርብቶ አደሩን ከቀዬው እና ከእርሻው ያለምንም አማራጭ በኢንቨስትመንት እና መሰረተ ልማት ስም በማፈናቀል ዘመናዊ የጭሰኛ ስርዓት የፈጠረ የኢኮኖሚ እድገት በየትኛውም ሃገር ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም፡፡ በሃገሪቷ አራቱም አቅጣጫዎች ቢኬድ የድህነታቸውን ልክ ለመናገር የሚከብዱ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን መመልከት ከባድ አይደለም፡፡ ሞፈር ጨብጠው ስንዴ የዘገኑ እጆች ዛሬ ለስንዴ ልመና ተዘርግተዋል፡፡ ለተጠማኝ ወተት ያጠጡ ሽክናዎች ዛሬ ውሃ አጥተው ተሰቅለዋል፡፡ ላሞች እና ጥጆች ይቦርቁ የነበሩበት የግጦሽ መስክ ዛሬ ተሸንሽኖ ለመንግስት ወዳጆች እጅ መንሻ ውሏል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ የኢኮኖሚ ድቀት ከወዴት አለ? ታዲያ የግንቦት 20 ትሩፋት የሆነው የተበላሸ የኢኮኖሚ ስርዓት ሰላባ ያልሆነው ማን ይሆን?
ዳር ድንበር ለመጠበቅ ከበረሃ የዋለው ወታደር፣ ዳቦ ራበን ነፃነት እንደውሃ ጠማን የሚሉትን የሚያድነው ታዛዡ ፖሊስና ደህንነት፣ የህዝቦችን ሆድ ለመሙላት ላይ ታች የሚለው አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር፣ የህዝቦች የእውቀት አባት የሆነው መምህር፣ የህዝቦችን ጤና ለመጠበቅ የሚባትለው የጤና ባለሙያ፣ ዘመኑን በትምህርት አሳልፎ ስራ አጥ የሆነው ወጣት… ወዘተ ሁሉም በአንድነት በስቃይ የሚማቅቁበት ሃገራዊ ፍቅራቸው የተሸረሸረበት የተረገመ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዴት ማደግ ይቻለዋል?

ትላንትም ዛሬም የዳቦ ጥያቄ መልሱ ጥይት ነው፡፡ ትላንትም ዛሬም የነፃነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄ መልሱ እስር እና ግድያ ነው፡፡ ምንም ለውጥ የለም፡፡ ታዲያ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይኖር የኢኮኖሚ ለውጥን እንዴት ማሰብ ይቻል ይሆን?

በመጨረሻም ድህነት የቁጥር ሳይሆን የተግባር መፍትሔ ያሻል፡፡ ማንነታችን ይመስል ድህነት ለረጅም ጊዜ አብሮን ቢኖርም ብቸኛው መፍትሔ ድህንቱን ከቤተመንግስቱ በላይ ጥበቃ የሚያቆምለትን ስረዓት ማስወገድ ነው፡፡ ድህነት በሁለት መንገድ ማስወገድ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከደሃው ነጥሎ ድህነትን ማስወገድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የወያኔ መንግስት በይፋ እየተገበረው ያለው ደሃን ከነድህንቱ በማጥፋት ድህነትን ማጥፋት ነው፡፡ ይህንን መፍትሔ ተግባራዊ የሚያደርጉ ገዚዎቻችን ድህነት ማንነት ነው ብለው ያመኑ ስለሆኑ ነው፡፡


ያላደገ አስተሳሰብ ያደገ ኢኮኖሚ ሊፈጥር አይቻለውም!!!
ቁጥሩ ለተራበ ሰው ዳቦ አይሆን!!!
ስለፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገት ሲባል ይህ ስርዓት-አልባ ስርዓት ይፍረስ!!!
የሳምንት ሰው ይበለን!!! 

No comments:

Post a Comment