Wednesday, 11 June 2014

የእሳት ልጅ ጤዛ



የእሳት ልጅ ጤዛ
መቅደላ ይሉት ፅላት ላይ
ኢትዮጲያ ይሏት ስውር እጅ
በእሳት ልሳን ስትከትብ ሰታኖር የማይጠፋ ቃል
የነብይ እንቦቀቅላ እጆቹን ሽቅብ ዘርግቶ
የታሪክ እውነት ይሞቃል፡፡
እናቱ አገር ልታርቅ
የሞቀ እልፍኟን ጣጥላ ነብዩን በፍቅር አንቃ
እድሜዋን ስትንከራተት
ቀርታለች ካውላላው ሜዳ ወድቃለች ዳግም ላትነቃ
እማማ ደርባባ እመቤት የፍቅር ማማ ብርሃን ….
የፍቅር ፅንስ ራብተኛ የእረፍት ስይታም መሃን
‹‹
ይቅርብኝ የንጉስ ማእድ ውዴን የበላ ጅብ ይብላኝ
ጣረሞት ካሳን ቢጠራ ሳይነጥል እኔንም ይጥራኝ!››
በሰው በፈጣሪ ፊት የቃል ኪዳኗን አክብራ
ተዋቡ መንገድ ቀርታለች አንባው ጫፍ ላይ በውብ ፀዳል በናትነት ሳታበራ !
ባይኖቿ ካሳን እያየች
‹‹
ከሞት አድነኝ አኑረኝ ››
ስትለው በሃዘን ሲቃ!
ስለፍቅር ወንድነት ነጥፎ
ነፍሱ ከውዱ ነፍስ እኩል
በፍቅር ምጡ ተጨንቃ
እነዛ ትንታግ እጆቹ እየተንቀጠቀጡ
አይኖቹ መድህን ፍለጋ ከምድር ሰማይ ሲናጡ
ከእውነት ቁንጮ ሳትደርስ በክናዱ ላይ እንዳለች
ያች የፍቅር ፀዳል ተዋቡ መንገድ ቀርታለች!
ያች የፀደይ ፀሃይ ተዋቡ በጧት ጠልቃለች!
መቅደላ ይሉት ፅላት ላይ
ኢትዮጲያ ይሏት ስውር እጅ
በእሳት ልሳን ስትከትብ ስታኖር የማይጠፋ ቃል
የነብይ እንቦቀቅላ
እጆቹን ሽቅብ ዘርግቶ
የታሪክ እውነት ይሞቃል
ይሄ ከርታታ አባቱ
በቀኙ እጁ የመዳፍ ጥርስ ሽጉጡን እንደነከሰ
በግራው የልጁን እራስ በፍቅር እየዳበሰ
‹‹
አለሜ ራበህ እንዴ ›› ይለዋል በፍቅር ቃሉ
ከአባትና ልጅ ማዶ
በእንግሊዝ የመድፍ አረር እልፍ ጦቢያኖች ያልቃሉ
የእውነት ልጆች ስለሃቅ ከአንባው ስር ይዋደቃሉ
ገብርየ ቁልቁል ሲጋልብ የልብሱ ቀለም ከሩቁ ስንብት ይፈነጥቃል
የእሳት ጅራፍ ከፊቱ ሞት ሊድር ይፈነድቃል
ንጉሱ የቀረውን ሃቅ አንድ ነፍሱን ሊሰዋላት
ከአንባው ጫፍ ሽጉጥ ጨብጦ አገሩን አሻግሮ ሲያያት
እንደኩሩ ወይዘሮ ምድሯ ለምለም ቀሚስ ለብሶ
ለባእድ ያጎበድዳል ወኔዋ በፍራት ፈሶ
‹‹
ምን ዋጋ አለው መልክ ቢያምር ቢሽቆጠቆጥ ልምላሜ
ምድሯ የእውነቷ መንበር መንፈሷ ካልሆነኝ ደሜ ››
የሚል የውስጥ ዋይታው ከአንባው እያስተጋባ
በዝምታው ጥልቅ ባህር ለትውልድ መተላለፊያ የሃቅ ድልድይ ሲገነባ
አለማየሁን ከኋላው አገሩን ከፊት አድርጎ
አይጠላት የልጁ ምድር አይወዳት የጠላት ድርጎ
ግራ ገብቶት እንደቆመ የመድፍ አረር እያፏጨ
ቁልቁል ይወነጨፋል ያለቱን ጥግ እየገጨ
በሞትና እውነት መሃል ስንዝር ሲቀር ውድቀት ሊባጅ
የቴውድሮስ እጅ ቃታ ሲያጠብቅ ለታሪክ ሊነግር አዋጅ
‹‹
አባባ›› ይላል ከኋላው የነብዩ እንቦቀቅላ
በእሳት መሃል የበቀለ የጀግናው ቴውድሮስ መሃላ!
መቅደላ ይሉት ፅላት ላይ
ኢትዮጲያ ይሏት ስውር እጅ
በእሳት ስትከትብ ቃል
የነብይ እንቦቀቅላ
እጆቹን ሽቅብ ዘርግቶ
የታሪክ እውነት ይሞቃል
እንቦቀቅላው ሲባንን መቅደላን ባእድ ረግጧታል
ምድሯ በታሪክ ቁሸት እንደቁሪሳ ጠንብቷል
ነበር ያሉት እውነት ሁሉ ከእውነት አንባ ቁልቁል ሸሽቷል!
ድፍን ጦቢያ እንደማድ ቤት ጥጋ ጥጓ በጥቁር ቀን በመደፈር ጭሽ ጠልሽቷል
ከአንባው ጫፍ ከእውነት ጥግ . . . ብቸኛው እንቦቀቅላ
ከትንታግ አባቱ ሬሳ ተደፍቶ እያለቀሰ
የጦቢያን ቀንዲል ጉልላት ደም ያጨቀየው ሽሩባ በሃዘን እየዳበሰ
የመቅደላን አምባ ጥሶ የመደፈር ዲቃላ ቃል ልኡል አጠገብ ደረሰ!
በባእድ መዳፍ ጉተታ ሽቅብ ተስቦ ሲነሳ
የጨቅላ እጁ ሙጥኝ ብሎ ካባቱ ትኩስ ሬሳ
ደም ያጨቀየው ሹርባ ከደም ጋር የተገመደ
ህብረትን አደራ እያለው ህፃኑ ቁልቁል ወረደ
የተሰበረ ልጅ ቅስሙ በደራሽ ጎርፍ ውስጡ ሟሙቶ
የሳት ልጅ ጤዛ ሆነና ተነነ የሰው ቀን ነግቶ
የቀን ቅንነት ሲጎድል ተወልዶ እውነት ከሸሸ
የምቦቀቅላው ማለዳ ሳያረፍድ ንጋት ላይ መሸ!!

Alex Abreha

No comments:

Post a Comment