Sunday, 27 July 2014

የመንግስት የሽብር ዕቅድ እንዲሳካ አንፈቅድም! የዒድ ተቃውሞ ተሰርዟል!



እሁድ ሐምሌ 20/2006 በሃምሌ 11 ‹‹የጥቁር ሽብር›› ቀን የሙስሊሙ ማህበረሰብ ትግል ፍጹም ሰላማዊነት ሰላም የነሳው መንግስት አሳፋሪና ታሪክ የማይረሳው የሃይል እርምጃ ወስዷል፡፡ ይህንኑ እብሪቱን በመቀጠል አሁንም በተመሳሳይ መልኩ የኢድ ቀን ተቃውሞ ላይ ከፍተኛ ብጥብጥና ሽብር አስነስቶ የሰው ህይወት በማጥፋት እንቅስቃሴያችንን ለማጠልሽት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ዒድ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲኖር ታቅዶ የነበረውን ተቃውሞ በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች መሰረዝ አስፈላጊ ሆኗል፡፡

1.   በመጀመርያ ደረጃ እንቅስቃሴያችንን ምንጊዜም ሰላማዊና የሰላም ወዳዱ ህዝባችንን ባህልና ክብር የጠበቀ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ከህዝባችን ባህል እና ክብር ተፃራሪ የሆነ ተግባር ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ካለው መንግስት ጋር በእኩል ደረጃ መገመት ለህዝባችንም ለእንቅስቃሴያችንም የማይመጥን በመሆኑና ለመንግስትም ያሰበውን እንዲያሳካ እድል መስጠት አስፈላጊ ባለመሆኑ፤
2.   ‹‹ጥቂቶች›› እያለ ራሱን የሚያታልለው መንግስት በዒድ የሚኖረውን ግዙፍ ህዝባዊ ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ በመስጋት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ በጣም አስተማማኝ መረጃ በመገኘቱ፤ በአሁኑ ወቅትም በመንግስት አካላት እየተካሄደ ያለው ውይይት ‹‹የምንወስደው እርምጃ በዱላ ይሁን ወይንስ በጥይት?›› የሚለው እንጂ የሃይል እርምጃ መውሰዱ አማራጭ የሌለው እንደሆነ ከውሳኔ መድረሱን በማረጋገጣችን፤
3.   በመቀጠልም መንግስት ለራሱ የከሰረ የፖለቲካ ጥቅም ለመገብየት ደፋ ቀና የሚልበትን እኩይ እቅዱን ለማክሸፍና ይህንን ለማድረግ ያበቃውን ግዙፍ እንቅስቃሴ በመንግስት እርምጃ እና ማዋከብ ተቻኩሎ ረጅሙን ጉዟችንን በአጭር ትንፋሽ እንድንጨርስ የሚያደርጉ ማናቸውንም በሮች መዝጋት በማስፈለጉ፤
4.   መንግስት በሙስሊሙ ላይ ከፍተኛ ግፍ የፈፀመ ቢሆንም ሃገር ለማስተዳደር ኃላፊነት ወስጃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ከተግባሩ እንዲታቀብና አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ቆም ብለው እንዲያስቡበት ለማድረግ፤
5.   ላለፉት 3 አመታት ብዙ ችግሮችን ተቋቁመን ሰላማዊነታችንን ያስመሰከርን በመሆኑና አሁንም በዚሁ መርሃችን በመፅናት ሌሎች ዘርፈ ብዙና እስካሁን ድረስ ያልተሞከሩ ስልቶችን ደረጃ በደረጃ መተግበር የበለጠ ውጤታማ ያደርገናል ብለን በማመናችን፡፡
ስለሆነም ህብረተሰቡ የኢድ ቀን ምንም ተቃውሞ እንደሌለ በመገንዘብ ከዘመድ አዝማድ ጥየቃ በተጨማሪ ‹‹ጥቁሩ ሽብር›› የተጎዱ ሰዎችን በመዘየርና እገዛ የሚፈልጉትንም በመርዳት እንዲያሳልፈው ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ወደ ሰላት በምንሄድበትም ሆነ በምንመለስበት ወቅት ከመንግስት አካላት ሊደርስ የሚችልን ማንኛውም ትንኮሳ በትዕግስት በማሳለፍ ብስለታችንን እናሳይ፤ የመንግስትን አላማም እናክሽፍ! በተጨማሪም እኛን መስለው በየአካባቢያችን ባሉ መስጊዶች በመግባት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ለአደጋ ለማጋለጥና ለመከፋፈል ከሚሞክሩ የመንግስት ሀይሎች ራሳችንን እንጠብቅ!
በዒድ ቀን በጋራ አንድነታችንን፤ ሰላም ወዳድነታችንን፤ ለእንቅስቃሴው ያለንን ክብርና ታዛዥነታችንን በማሳየት ለቀጣዩ ዘርፈ ብዙ ትግል እንዘጋጅ!
ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከ ድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Wednesday, 23 July 2014

ማነው የታሰረው?



 
አቦ ታሰረች፣ ታሰረች፣ ታሰረች፣ ታሰረች አትበሉኝ!!!

እኛ ሰልፍ አትውጡ ስንባል ከቤታችን የማንወጣ፣ እጅ ስጡ ስንባል እግራችንንም የምንመርቅ፣ አትፃፉ ስንባል ብዕራችንን የምናስረክብ፣ አትዩ ስንባል አይናችንን ጨፍነን ጀሮአችንን የምንይዝ  ያለእጅ የታፈንን እና ያለካቴና የታሰርን እያለን እርሷ ታሰረች አትበሉኝ፡፡

እርሷማ እንኳን ደስ ያለን ነፃ ወጣች እንጂ አልታሰረችም፡፡ በብርታቷ፣ በፅናቷ እና በጀግንነቷ ነፃ ወጣች፡፡ እርሷማ ነፃነቷ በደሟ የዋጀችና በእጇ ስብራት የባርነት ቀንበርን የሰበረች ጀግና ናት፡፡ እርሷማ አካላዊ መከራን ተቀብላ መንፈሳዊ ነፃነቷን አገኘች፡፡ 

ታዲያ የትኛው ነው የነፃነት መንገድ? የወይኒ መንገድ ወይስ አሁን እኛ ያለንበት መንገድ?

ዲሞክራሲን እንጂ ነፃነታችንን ከምርጫ ኮሮጆ አንጠብቅ፡፡ ነፃነት ሳይኖር ዲሞክራሲ ሊኖር አይችልም፡፡ ነፃነትን ለማግኘት አቅጣጫችንን ወደ ቤተመንግስት ሳይሆን ወደ እስር ቤቶች እናድርግ፡፡ ‹‹የነፃነት ጉዞ ወደ እስር ቤት›› ብለን እናውጅ፡፡ እንሂድ እስር ቤትን እንሙላ፡፡ በዚህ ወቅት ‹‹አቤቱ ጓደኛዬን ፍታልኝ›› የሚል የፈሪ ፀሎት አይሰራም፡፡
የነፃነት ጉዞ ወደ እስር ቤት