Saturday, 19 July 2014

ጥያቄው እና መልሱ



ጥያቄው የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ጥያቄ መሆኑን ማንኛችንም ልንክድ የማንችለው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ሃይማኖታዊ ጥያቄ መንግስት የሰጠው በሃይል የተደገፈ ፖለቲካዊ ምላሽ ማንኛችንም ልንቀበለው ወይም ልንታገሰው የማንችለው ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ነው፡፡ ይህንን ለመቃወም ሙስሊም መሆን አያስፈልገንም፡፡ ይህንን ለመቃወም የፓርቲ አባል መሆን አያስፈልገንም፡፡ ይህንን ለመቃወም ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት ወይም ካቶሊክ መሆን አያስፈልገንም፡፡ ይህንን ድርጊት ለማውገዝ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡

እኔ ይህንን መንግስት በማን አለብኝነት የሚከውነው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመቃወም የእስልምና ሃይማኖቱ ተከታይ መሆን አይጠበቅብኝም፡፡ እኔ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ነኝ፡፡ ነገር ግን በሙስሊም ወንድሞች እና እህቶች ላይ የሚወሰደው ኢ-ፍትሃዊ እርምጃን እቃወማለሁ፡፡ ዛሬ በሙስሊሞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ሙስሊም ስላልሆንኩ ብዬ ዝም ካልኩ ነገ በእኔ ሃይማኖት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈፀም መንገዱን እየጠረግኩ ነው ማለት ነው፡፡

ሁላችንም ልናውቅ የሚገባው ጉዳይ የሰው ልጅ በቡድንም ሆነ በግል ማንኛውንም ጥያቄ የማንሳት መብት አንዳለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የማንሳት መብት ላይ ምንም አይነት ገደብ ሊጣልበት አይገባም፡፡ ጥያቄያቸው ተገቢም ሆነ አልሆነ መንግስት ጆሮ ሊሰጣቸው ብሎም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የዜጎችን ጥያቄ የማፈን ድርጊት ወደ አላስፈላጊ ግጭት ሊያመራ ይችላል፡፡ ለዚህም አፋኙ አካል ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነቱን ይወስዳል፡፡ ይህም ማለት በአንዋር መስጊድ በመንግስት ትዕዛዝ የፀጥታ ሃይሎች ላደረሱት እና ለደረሰባቸው አካላዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መንግስት ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነቱን መወሰድ ይገባዋል፡፡

ሌላኛው እዚህ ጋር ማንሳትና ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ጉዳይ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ምንም አይነት የህግ አግባብ ወይም ክፍተት አለመኖሩን ነው፡፡ ሙስሊሞች በመጀመሪያ ያነሱት ጥያቄ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄያቸው ያለምንም መንግስታዊ ጣልቃ ገብነት ሃይማኖታዊ ምላሽ ብቻ ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግስት ህዝበ ሙስሊሙ ላነሳው ሃይማኖታዊ ጥያቄ የሰጠው ፖለቲካዊ ምላሽ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ፖለቲካዊ ምላሽ ወይም ፖለቲካዊ ጥያቄ ሃይማኖታዊ ምላሽ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በቦታው ላይ ተገኝቶ መንግስት ተብዬው አካል የሙስሊሙን ጥያቄ ያስተናገደበትን ኢ-ፍትሃዊ እና ኢ-ሰብዓዊ ሁኔታ የመቃወም እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን የማሰማት ህጋዊ መብት እና ግዴታ አለው፡፡ በእስር እና በድብደባ ጥያቄውን ለመመለስ መሞከር ሌላ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ከማስከተል የዘለለ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ እዚህ ላይ ወይንሸትም (የሰማያዊ ፓርቲ አባል) ሆነች ጌታቸው (ጋዜጠኛ) በቦታው ላይ ለመገኘት ሰው ከመሆን ውጪ ሌላ ተጨማሪ ምክኒያት አያስፈልጋቸውም፡፡ ሰዋዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሰዋዊ ግዴታቸውን ነው የተወጡት፡፡

በእለቱ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ተቀደሰው መስጊድ መግባታቸው ምንም አይነት አግባብ የለውም፡፡ ይህም መንግስት ለሃይማኖቶች ምንም አይነት ክብር የሌለው ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በየ ቤተ-ሃይማኖቱ የተሰገሰጉ ከፈጣሪያቸው በላይ ለስርዓቱ የተንበረከኩ የበግ ለምድ የለበሱ ባለ ጥምጣም እና ቆብ ካድሬዎች ቤተ አምልኮዎችን አርክሰዋቸዋል እንዲሁም የመንግስት ፖለቲካ መፈንጫ አድርገዋቸዋል፡፡ ስለዚህም በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የተሰገሰጉ የመንግስት ካድሬዎችን ከየ ቤተ-እምነቱ የማጥራቱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሃይማኖታዊ ጃንጥላቸውን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ከሚጠቀሙ የመንግስት ካድሬዎችን የፀዳ የሃይማኖት ተቋሞች ሊኖሩን ይገባል፡፡

በመጨረሻም በዚህ ሰላማዊ ትግል መከራ እና ስቃይን ለተቀበላችሁ ሁሉ አክብሮቴን፣ አድናቆቴ እና ድጋፌን እየገለጥኩ ይህንን መልዕክቴን በማርቲን ኒሞለር አባባል ላጠቃለው፡፡ ማርቲን ‹‹ናዚዎች በመጀመሪያ ሶሻሊስቶችን መያዝ ጀመሩ፤ ምን ቸገረኝ ሶሻሊስት አይደለሁ አልኩ፡፡ ቀጥሎም የሰራተኛ ማህበር መሪዎችን መያዝ ጀመሩ፤ ምን ቸገረኝ የሰራተኛ ማህበር አባል አይደለሁ አልኩ፡፡ ቀጥሎ ካቶሊኮችን መያዝ ጀመሩ፤ ምን ቸገረኝ ካቶሊክ አይደለሁ አልኩ፡፡  በመጨረሻም እኔን ሲይዙኝ ሌሎቹ ‘ምን ቸገረን’ እሱን አይደለን ሲሉ ሰማኋቸው›› ነበር ያለው፡፡ ስለዚህ ወዳጆቼ ችግሩን ዝም ካልን መጨረሻውን ማምለጥ በማንችልበት ግለሰባዊ ደረጃ ላይ መውረዱ ስለማይቀር ቀድመን ልንታገለው ይገባል፡፡

ክብር እና ሰላም ከእናንተ ጋር ትሁን!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!  

                       

No comments:

Post a Comment