Friday, 16 May 2014

የኢትዮጵያ ራዕይ


ስራህንና ድካምህን ትዕግስትህንም አውቃለሁ፡፡ ክፉዎችን ልትታገስ እንደማትችል እንዲሁም ሳይሆኑ ዲሞከራሲያዊ መንግስት ነን የሚሉትን መርምረህ ሃሰተኛ ደም መጣጭ አምባገነኖች (ዲሞንክራት ወይም ሰይጣናዊ ገዢዎች) ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፡፡ ታግሰህማል፡፡ ስለ እኔም ብለህ ሁሉን ችለህ ለማለፍ ሞክረሃል፡፡ ዳሩ ግን የምነቅፍህ ነገር አለኝ፡፡
ልጄ፤ የቀደመውን ፍቅርህን እና የአባቶችህን ጀግንነት ትተሃል፡፡ እንግዲያው ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፡፡ የቀደመውን ሃገራዊ እና ወገናዊ ፍቅርህን እንዲሁም የአባቶችህን ጀግንነት ከጣልክበት አንሳ፡፡ ይህንን ባታደርግ ግን ሃገርህ እንዳገር ለመቀጠል በማትችልበት ደረጃ ላይ የምታደርገውን የቁልቁለት ጉዞ እንዳገዝክ እቆጥርብሃለው፡፡ ሃገርህን ለማውደም የጎሰኞች ጎጆ ለቀለሱት እና አሁንም ጎጆዋቸውን በማስፋፋት ላይ ለሚገኙት ምሰሶ እና ማገር አቀባይ በመሆን ያጎረሰህን እጄን እና ያጠባህ ጡቴን እንዳትነክስ ተጠንቀቅ፡፡ የእኔን የእናታቸውን ደም ለሚመጡ፣ ስጋዬን ለሚቆርጡ እና አጥንቴን ለሚግጡ ዘረኛ አምባገነኖች ቢላዋ ስሎ ከሚያቀርቡት ወገን እንዳትሆንም አበክረህ እራስህን ጠብቅ፡፡
መከራህን ድህነትህንም አውቃለሁ፡፡ ገዢዎችህ ባንተ ጫንቃ ላይ ባለጠጋ እንደሆኑም አውቃለሁ፡፡ እነርሱ የሰይጣን ማህበርተኞች ናቸው፡፡ ስለእኔ ስለእናትህ ብለህ ልትቀበለው የምትችለውን መከራ አትፍራ፡፡ ልትፈራ የሚገባህ ሕይወትህን ያለክብርንዳትመራ ነዉንጂ ክብር የተነፈገዉ ሕይወትህንንዳታጣ መሆን የለበትም፡፡
እኔ ከዚያ በላይ መከራንና ስቃይን ስለእናንተ ልጆቼ ስል ተቀብያለሁ፡፡ ለእኔ ውሃ ሳይኖረኝ በውሃ ጥም እየተቃጠልኩ ለእናንተ ለልጆቼ ውሃን ሰጥቻለሁ፡፡ እኔ በረሃብ እየተቃጠልኩ እናንተን የእናትነት ጡቴ እስኪነጥፍ እንዲሁም አጥንቴ እስኪገጥ ድረስ መግቤያለሁ፡፡ ገዢዎቻችሁ እናንተ እንድትፈተኑ ከእናንተ አንዳንዶቹን እየመረጡ በወህኒ ያማቅቃሉ፡፡ የከፋ መከራንና ስቃይን እንዲቀበሉ ያደርጋሉ፡፡ ያሻቸውንም በአደባባይ የሌሎች መማሪያ ይሆኑ ዘንድ ይገድላሉ፡፡ ነገር ግን እናንተ እስከ ሞት ድረስ ስለ እኔ የታመናችሁ ሁኑ፡፡
የአምባገነኖች ዙፋን ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንደምትኖሩ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ስሜን ለመጠበቅ የምታደርጉትን ጥረት አውቃለሁ፡፡ ጨፍጫፊ መንግስት በሚኖርበት ስለኢትዮጵያዊነታችሁ በተገደላችሁበት በዚህ ዘመን እንኳ ኢትዮጵያዊነታችሁን አልካዳችሁም፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊነት ለከፈላችሁት መሰዋዕትነት ስለ እኔ እናታችሁ ክብር ላፈሰሳችሁት የደሜ ምጣጭ የሆነው ክቡር ደማችሁ አምባገነኖችን ድል ለሚነሳው ኢትዮጵያዊ ማንነታችሁ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፡፡
ስራችሁና ፍቅራችሁን እምነታችሁንም፣ አገልግሎታችሁንም እንዲሁም ትዕግስታችሁንም ከፊተኛውም ስራ ይልቅ የኋለኛው እንዳበዛባችሁ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ ነኝ የሚለውንና እናንተ ልጆቼን ሱሰኝነት እና ሴሰኝነትን የሚያስተምረውን እና ትውልድን የሚያስተውን ኢህአዴጋዊ ስርዓት እንዲስፋፋ ፈቅዳችኋልና የምነቅፋችሁ ነገር አለኝ፡፡
ይህ ስርዓት እንዲስተካከል ጊዜ ሰጠሁት፡፡ ነገር ግን ከአፀያፊ ተግባሩ ለመታቀብ አልወደደም፡፡ እነሆ፤ በእናንተ ልጆቼ ብርቱ ክርን ከስልጣን እርካቡ ላይ እጥለዋለሁ፡፡ ከዚህም ስርዓት ጋር የሚያመነዝሩትንም ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ በታላቅ መከራ ላይ እጥላቸዋለው፡፡ ለእያንዳንዳቸው እንደ ስራቸው እሰጣችኋለው፡፡ ነገር ግን ስለ ኢትዮጵያዊነት መከራን ለተቀበላችሁ ለእናንተ ግን እውነት እውነት እላችኋለው ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፡፡ በስሜ ያላችሁን ክብር እና ፍቅር ጠብቁ፡፡ አምባገነኖችን ድል ለነሳውና እስከ መጨረሻው ስሜን ለጠበቀው የእኩልነት ስልጣን በትርን በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፡፡
ዛሬ ስለኢትዮጵያዊነት እና ስለእውነት የበላይነት በይፋ መከራን የተቀበላችሁ እና እየተቀበላችሁ ያላችሁ ጥቂት እንደሆናችሁም አውቃለሁ፡፡ እውነት ብዙ ሰው ስለተከተላት ሳይሆን እውነት እውነት ስለሆነች ብቻ ታሸንፋለች፡፡ ልጆቼ ሆይ፤ እውነት አምባገነኖች ከታጠቁት ከማንኛውም መሳሪያ በላይ ነው፡፡ ስለያዛችሁት እውነት እንጂ አምባገነኖች ስላነገቱት መሳሪያ አትጨነቁ፡፡
የብረት ልብስ የለበሰውና መሳሪያ የታጠቀው ጎልያድ እራፊ ጨርቅ በለበሰውና ወንጭፍ በታጠቀው ብላቴናው ዳዊት ጠጠር ተሸንፏል፡፡ ጎልያድን ያክል ግዙፍ የጦር ሜዳ ጀግና የጣለችው ከዳዊት ወንጭፍ የተወረወረች ጠጠር አይደለችም፡፡ ጠጠሯ የዳዊት እውነቱ እና እምነቱ ነች፡፡ የጎልያድ ብርቱ ክርን፣ የለበሰው የብረት ልብስ እና የታጠቀው መሳሪያ በዳዊት የእውነት እና የእምነት ባሩድ ከተሞላች ጠጠር አላዳነውም፡፡ ጎልያድን ያክል በሃይሉ የሚተማመን ታላቅ መሪ በህፃኑ ዳዊት እውነት ተሸንፏል፡፡
የያዛችሁት እውነት እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላችሁ እምነት ብቻ ነፃ ለመውጣት በቂ ነው፡፡ እውነት የያዘ ሰው አይፈራም፡፡ ከፍርሃት በላይ ክፉ ጠላት የለም፡፡ እውነት እና ኢትዮጵያዊነትን ይዞ ፍርሃት ሚባል ነገር የለም፡፡ ከአድዋ በፊትም ሆነ በኋላ መሳሪያ የታጠቁ ጠላቶቻችንን ያሸነፍንበት ዋነኛ መሳሪያ እውነት እና በጀግንነት የተዋጀ ሃገራዊ ፍቅር ነው፡፡
አላማ ያለው ሰው አይሸነፍም፡፡ እስራኤላውያንን ነፃ ያወጣውን ሙሴን ተመልከቱት፡፡ እስራኤላውያንን ከባርነት የማውጣት አላማ ነበረው፡፡ ህዝቡ ግን በባርነት መኖርን እንደግዴታው የተቀበለ ስለነበር ለሙሴ ድጋፉን ለመስጠት ያመነታ ነበር፡፡ አሳዳሪዎቻቸውም የሙሴን እውነት እና እምነት ለመረዳት እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ታግለው ነበር፡፡
ሙሴ እውነት እንደያዘ ለግብፅ ፈርኦኖች ለማሳየት የእውነት በትሩን መሬት ላይ ጣለ፡፡ በትሩም ወደ እባብነት ተቀየረ፡፡ የፈረኦን ውሸት አንጋች አስማተኞችም የውሽት በትራቸውን ጣሉና ወደ እባብ ቀየሩ፡፡ የሙሴ እባብ ግን የአስማተኞቹን እባብ በላች፡፡ ውሸት በነገሰበት ምድር የእውነትን የበላይነት አስመሰከረ፡፡ ነገር ግን ውሸት አንጋቾቹ የሙሴን እውነትን የበላይነት ለመረዳት ወይም ለመቀበል አልቻሉም ወይም አልፈለጉም፡፡ ይህም እልቂትን አስከተለ፡፡ ከእልቂቱም በኋላ ውሸት አንጋቹ ፈረኦን ህዝቡ በነፃነት እንዲሄድ ፈቀደ፡፡
በዚህም ሰዓት የውሸት አንጋቾቹ ልብ ውስጥ ያለችው ውሽት በሙሴ እውነት አልተሸነፈችም ነበርና በሙሴ መሪነት የእስራኤል ህዝብ የሚያደርገውን የነፃነት ጉዞ ለማደናቀፍ ጦር እና ሰረገላቸውን ከኋላቸው አንቀሳቀሱ፡፡ ነገር ግን እንኳን የአንባገነኖች በውሸት የተሞላ ጦር እና ሰረገላ ይቅርና ግዑዙና ታላቁ ቀይ ባህር ሳይቀር ስለ እውነት ተንበረከከ፡፡ ሙሴ ባህሩን በእውነት በትር መታው፡፡ ባህሩም በእውነት ስለእውነት ሲል በሁለት ተገመሰ፡፡ የሙሴ እውነት ተከታዮችም በተገመሰው ባህር ተሻገሩ፡፡ ስለዚህ የያዛችሁት እውነት የአምባገነን ስርዓትን ብቻ ሳይሆን ባህርን ለሁለት ገምሶ ከባርነት ነፃ ያወጣል፡፡ እውነት አምባገነን ስርዓትን ብቻ ሳይሆን ባህርን እንደ ግርግዳ ያቆማል፡፡
ስለዚህ እናንተ ጎረቤት ወዳጅ በመሆን በምትኖሩባት መሬት ላይ ኑሮን የምትካፈሉ ብቻ ሳንሆን ከአያት ቅድመ አያታችሁ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ አንድ ደም የተቀዳችሁ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናችሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነታችሁ ለሙሐመድ ለሙሴና ለክርስቶስ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቆ የሚደባለቅበት እምነት ነው፡፡ ይህ እምነታችሁ ከገዢዎች የሚለገስ ወይም የሚከለከል ሳይሆን ፈጣሪ ከእኔ አብራክ ስትወለዱ ጀምሮ የተሰጣችሁ የራሳችሁ የሆነ ማንም ሊደፍረው የማይችል መብታችሁ ነው፡፡
በአበሻ ምድር ተቻችሎ መኖር ከጥንት ጀምሮ የኖረና ወደፊትም መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ተከታዮቻቸው ወደ እኔ መጥተው ሰላምንና ዕረፍትን እንዲያገኙ ሲመክሩ ይህንን ያሉት እኔ ዘንድ ክርስቲያኖች እንዳሉ ሳያውቁ ቀርተው ነው ለማለት አልደፍርም፡፡ ይልቁንም ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር የአበሻ አገር ምቹ እንደሆነ አስቀድመው ስላወቁ ነው እንጂ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኖረው ይህ መከባበር ምንም እንኳን በተለያየ ጊዜ በገዢዎች ተጽዕኖ ሥር በመውደቁ አንዴ ሲጠብቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲላላ ቢሄድም እስካሁን ሳይበጠስ እናንተ ልጆቼ ዘንድ ደርሷል፡፡
የሳምንት ሰው ይበለን!!
       

የሚታገሉትን የማያውቁ ታጋዮች





የተቃዋሚ ባንዲራ ማውለብለብ እና በተቃዋሚ ፓርቲ ጃንጥላ ስር መጠለል ብቻ ተቃዋሚ አያሰኝም፡፡ የሰማያዊንም ሆነ የአንድነትን ባንዲራ እያውለበለቡ ከወያኔ አስተሳሰብ የማይለይ አስተሳሰብ የሚያራምዱ መኖራቸውን የሚካድ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ትግል ከመጀመሩ (ከመታሰቡ) በፊት ‹‹ማንን፣ ለምን እና እንዴት ነው የምንታገለው?›› ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

የምንታገለው ኢህአዴግን ወይስ አስተሳሰቡን?
እኔ የምታገለው አስተሳሰብን ነው፡፡ ማሸነፍም የምፈልገው አስተሳሰቡን ነው፡፡ ኢህዴጋዊ አስተሳሰብን ማሸነፍ ካቻልን ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ መወገድ አለበት፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኢህአዴግ ውስጥ ብቻ ነው ያሉት ብሎ ማመን የዋህነት ሳይሆን ጅልነትም ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ቡድን ሰማያዊም ሆነ አንድነት ውስጥ ይኑር ኢህአዴግ ውስጥ ካለው ባልተለየ መልኩ መታገል ተገቢ ነው፡፡

ይህ ካልሆነ የምንታገለው ‹‹ለምን እነርሱ ብቻ 23 አመት ሙሉ ጨቆኑን?›› ከሚል ሰንካላ እኩይ አስተሳሰብ በመነሳት ጨቋኝን በሌላ ጨቋኝ መተካትን አላማ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዋጋ የሌለው ምንም አይነት መሰዋዕትነት ሊከፈልበት የማይገባ ትግል ነው፡፡ ይህንን አይነት ትግል ደግሞ የትም አያደርስም፡፡

ስንታገል ‹‹ይህንን ህዝብ እንዴት ከባርነት ነፃ እናውጣው?›› ከሚል መነሾ በመነሳት እንጂ እንዴት በዚህ ህዝብ ላይ ሌላ የባርነት ቀንበር እንጫንበት ከሚል አስተሳሰብ መነሳቱ ትርጉም የለውም፡፡ ህዝባችን ባርነት ሆነ አገዛዝ ብርቁ አይደለም፡፡ ህዝባችን የናፈቀው ነፃነት ነው፡፡ ነፃነት እንደ ውሃ የጠማው ህዝብ ነው ያለን፡፡

ህዝባችን ባርነት፣ ጎጠኝነት… አንገሽግሾታል፡፡