Wednesday, 7 May 2014

አንድነት እራሱን ያጥራ…



‹‹አንድነት ፓርቲ በጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ያለመገኘት መብት የለንም፡፡ የመገኘት ግዴታ አለብን፡፡ ስንገኝ ደግሞ ሁለት አማራጭ አለን፡፡ አንደኛው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደሰማያዊ አባልነታችን ነው፡፡ እንደ ሰማያዊ አንድነት ቤት ስንገኝ አይናቸው ደም የሚለብስ እና ፊታቸው የሚቀላ የአንድነት ፓርቲ አባሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለኢትዮጵያዊያን የረዘመ የጭቆና እና የባርነት ዘመንን የሚመኙ ናቸው፡፡ እንዚህን ሰዎች ላለማስከፋት ብለን ከምናምበት እና ከቆምንለት የመከባበር፣ የመቻቻል እና የመተባበር ፖለቲካ ቅንጣት ታክል ልናፈገፍግ አይገባም፡፡ በዚህ አቋማችን የሚደርስብንን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይኖርብናል፡፡…›› ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በፓርቲዬ ሰማያዊ ፅ/ቤት ወጣት የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት የአንድነትን ሰልፍ በተመለከተ የተናገርኩት ሃሳብ ነበር፡፡
እውነትም እንዳልኩት የባርነትን፣ የጭቆናን እና የአገዛዝ ስርዓት በሃገሪቷ እንዲቀጥል የሚመኙ የአንድነት የታይታ ፖለቲከኞች አይናቸው ደም ሲለብስ እና ፊታቸው ሲቀላ ብቻ ሳይሆን ምላሳቸውን መግራት እስኪቻላቸው ድረስ ስንተባተቡ ለተመለከተ ምን ያህል በውስጣቸው ስር የሰደደ የጥላቻ ፖለቲካ እንዳለ ለመረዳት ያስችላል፡፡
በእለቱ በሰማያዊ ቲ-ሸርት ያሸበረቁት የሰማያዊ ልኡክ ጡርንባውን እየነፋ በአከባቢው ሲገኝ በአንድነት ሰልፍ ላይ ለመገኘት የተሰበሰበው ህዝብ ፍፁም ልባዊ ደስታውን በጭብጨባ በማቀፍ ሲገልጽ የተመለከቱ ጥቂት የማይባሉ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አካላት አይናቸው ደም ሲለብስ እና ፊታቸው ሲቀላ ቢመለከቱም ከቆሙለት አላማ አንፃር ይህንን ችለው በቦታው ለመቀጠል ጥረት ቢያደርጉም የፓርቲው ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ግን ዝምታውን በመስበር የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነውን አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድን በመጥራት ‹‹የለበሳችሁትን ቲ-ሸርት አውልቁ ወይም አከባቢውን ለቃቹ ሂዱልን›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ አቶ ብርሃኑም ይህንኑ በቦታው ለታደሙ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በጥያቄ መልክ ‹‹ቲ-ሸርታችንን እናውልቅ ወይስ እንሂድ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡
አባላቱም በሙሉ ‹‹ለምን? አንድነት ለፓርቲዎች ያቀረበውን ጥሪ አክብረን ፓርቲያችንን ወክለን ነው በቦታው የተገኘነው›› በማለት ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡ በዚህ ሰዓት በአከባቢው የነበሩ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ጉዳዩን ከማረጋጋት ይልቅ የሚያባብሱ ንግግሮችን መናገር ጀመሩ፡፡ ‹‹በእናንተ ምክኒያት መታሰር አንፈልግም፣ አድዋ ድልድይ ላይ እንዳደረጋችሁት ፖሊስ ባልፈቀደላችሁ መንገድ እየሄዳችሁ ከፖሊስ ጋር ግጭት ውስጥ ትከቱናላችሁ፣….›› ሌሎችንም ብዙ ምክኒያቶችን በመዘርዘር ቲ-ሸርቱን ማውለቅ መፍትሄ መሆኑን ተናገሩ፡፡
በዚህ ሰዓት የሰማያዊ ፓርቲ ህግ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ይድነቃቸው፣ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል አቶ አቤል  እና እኔ በቀበና አከባቢ የሰልፉ ፕሮግራም እስኪጀመር በግሪን ቫሊ ሆቴል ሻይ እየጠጣን በነበረበት ወቅት የአቶ ይድነቃቸው ስልክ አቃጨለ፡፡ በሰልፉ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ያንዱ ስለነበር ‹‹ተጀምሯል ኑ›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ይሆናል ብለን ስልኩ ተነሳ፡፡ መልዕክቱ ግን የሁላችንንም አንገት ያሰበረ ‹‹ቲ-ሸርት ካላወለቃችሁ ብለው አባረሩን!!!›› የሚል ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር አፈርኩ፡፡ ወጣቶቹን ለማረጋጋት ከሞከርን በኋላ ለአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ወደሆኑት አቶ ሃብታሙ አያሌው ደውለን ‹‹ለምን?›› አልን፡፡ አቶ ሃብታሙም ‹‹ፍፁም ሊደረግ የማይገባው ስህተት ነው›› በማለት ገልፀው ለጊዜው በቦታው እንደሌሉ አሁን እየደረሱ ስለሆነ ሁኔታውን አጣርተው እንደሚያስተካክሉ ገልፀው ስልኩን ዘጋን፡፡
መልሰን በቦታው ለተገኙ አመራሮቻችን አቶ ሃብታሙ ያሉትን ነግረን ተረጋግተው እንዲጠብቁ ለመንገር ስንደውል የተባሉት የአንድነት ፓርቲ  ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በቦታው እንደነበሩ ነገሩን፡፡ አዘንን፡፡ ከመዋሸት ምክኒያታዊ መሆን ይሻላል፡፡ ‹‹በቃ!!! ግሪን ቫሊ ሆቴል ነው ያለነው፡፡ እዛው ኑ፡፡››
ፊታቸው በንዴት፣ በሃዘን እና ተስፋ በመቁረጥ ጠቁሮ ወጣቶቹን ስመለከት እጅግ በጣም አዘንኩ፡፡ አቶ ይድነቃቸው ወደ አንድነት ፓርቲ የድርጅት ጎዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ደውሎ የተፈጠረውን ሁኔታ በማስረዳት ላይ ነበረ፡፡ ‹‹ስለተባለው ሁኔታ ምንም አላውቅም፡፡ ተከስቶ ከሆነ ግን ፍፁም ስህተት ነው፡፡…›› በማለት ላይ እያሉ የሰማያዊ ፓርቲ የጥናት እና እስትራቴጂ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ እያስቤድ የተባሉትን ግለሰብ (አቶ ዳንኤል) እንዳናገሯቸው እና እርሳቸውም የድርጊቱ ደጋፊ መሆናቸውን ገለፁልን፡፡ የተባሉት ግለሰብ ግን በጉዳዩ ማንም እንዳላነጋገራቸው ገለፁልን፡፡ ውሸት ቁጥር 2 አትሉም፡፡
ከአከባቢው ከመሄዳችን በፊት እንደፓርቲ የተሰማንን ቅሬታ ለመግለፅ ወደ አንድነት ፓርቲ ፅ/ቤት እኔ፣ አቶ ይድነቃቸው (የህግ ጉዳይ ሃላፊ) እና አቶ እያስቤድ (የጥናት እና እስትራቴጂ ጉዳዮች ሃላፊ) በመንገድ ላይ ሁለት አባላትን ጨምረን አመራን፡፡ ወደ ፅህፈት ቤቱ መዳረሻ ላይ የአንድነት ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ተክሌን እና የፓርቲውን የውጪ ግንኙነት ሃላፊን ኢ/ር ዘለቀን አገኘናቸው፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ አስረድተን የመጣነው እንደፓርቲ የተሰማንን ሃዘን ገለጽንላቸው፡፡ ሁለቱም በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ማዘናቸውን ገልፀው፡፡ ይህንንም ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦች ፓርቲውን እንደማይወክሉ ገልፀው ወጣቶቹ በአቅራቢያው ካሉ ተመልሰው መምጣት እንደሚችሉ ገለጡ፡፡
እኔ የገረመኝ እንዚህ ሰዎች ችግሮቹ ሲፈጠሩ በቦታው አልነበሩ እንዴ? ተዉ ጥሪያችንን አክብረው እና መብታቸውን ተጠቅመው ነው የመጡት ለማለት ለምን ከበዳቸው? በስተመጨረሻ ማዘናቸውን እና ይህንንም ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦች ፓርቲውን እንደማይወክሉ መግለፃቸውን ባደንቅም ችግሩ በጊዜው ለመፍታት ባለመቻላቸው እጅግ አዝኛለሁ፡፡
‹‹እኛ የምንለብሰውን ልብስ እናንተ ናችሁ ምትመርጡልን? ያስተላለፋችሁትን ጥሪ ለፖለቲካ ተቋማት ሁሉ ነበር፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዳይገኝ ከፈለጋችሁ ለምን ከሰማያዊ ፓርቲ በስተቀር አላላችሁም?..›› የሚል ጥያቄን ስንሰነዝር የፓርቲውን የውጪ ግንኙነት ሃላፊን ኢ/ር ዘለቀ ‹‹ድርጊቱ ፓርቲያችንን የማይወክል ስህተት ነው›› የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በዚህ ወቅት አቶ ዳንኤል መጥተው ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ምንም ሳይሉ በጥድፊያ ከአከባቢው ተሰወሩ፡፡ በስልክ ባነጋገርናቸው ወቅት ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ማንንም አላናገረኩም›› ማለታቸው ነገር ግን አሁን ያነጋገራቸው ሰው በቦታው መኖሩ አሳፍሯቸው ይሆን?
በአከባቢው ላይ ከሚገኙ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ጋር እየተነጋገርን በነበረበት ወቅት  ዳዊት አስራደ የሚባል  ሙሉ ጥቁር ሱፍ የለበሰ እና ደረቱ ላይ የሰልፉ አስተባባሪ የሚል ባጅ የለጠፈ አንድነት አመራር ‹‹ቲ-ሸርቱን አውልቁ ማለታችን ትክክል ነው፡፡ እንደግለሰብ የመገኘት መብት እንጂ እንደፓርቲ ቲ-ሸርት ለብሳችሁ የመገኘት መብት የላችሁም›› በማለት እጅግ አሳፋሪ መልስ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት ተናገረ፡፡ ቅድም ፓርቲውን አይወክልም፣ ስህተት ነው፣… ሲሉ የነበሩ ግለሰቦች አሁንም ሰልፉን በማስተባበር ፓርቲውን የሚወክለው ግለሰብን ንግግር መግራት ተስኗቸው ዝምታን ሲመርጡ ስመለከት ‹‹ዘመነ ዝም አንልምን›› አስታወሰኝ፡፡
ለዚህ ወጣት አንድ ጥያቄ ብቻ ወረወርኩ፡፡ ‹‹የኢህአዴግ ቲ-ሸርት ለብሶ መገኘት ይቻላል?›› ወጣቱ ጊዜ ሳያባክን ‹‹ይቻላል፤ እሱንማ እንፈልገዋለን›› በማለት ቆፍጠን ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹የሰማያዊንስ ቲ-ሸርት? ሰማያዊን አትፈልጉትም?›› መልስ የለም፡፡ ከኢሰፓ ስብሰባ ቀጥሎ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከሸራተን ጋዝ ላይት ውጪ አለባበስ የሚመረጥበት ቦታ አለ ከተባለ የመጀመሪያው የአንድነት ሰልፍ ላይ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝ፡፡
አሁንም ልነግራችሁ የምፈልገው ዋነኛው ነገር እናንተ እኛን ከማባረረችሁ በፊት አቅፈው በጭብጨባ ስለተቀበሉን አባሎቻችሁ እና ደጋፊዎቻችሁ ክብር እና ፍቅር ስላለኝ የተፈፀመብን በደል የወያኔ መንግስት እንኳን ለማድረግ ያልደፈረውን ድርጊት ቢሆንም ፓርቲው ፈፀመብን ለማለት ድፍረት አጣለሁ፡፡ በተለይ የፓርቲው አመራሮች ከታይታ እና ተራ ሴራ ፖለቲከኝነት ካልወጡ የአንድነት ፓርቲ እንደፓርቲ ለመቀጠል ይቸገራል ብዬ አስባለሁ፡፡
እዚህ ጋር አንድ አዛውንት (አቶ ድንቁ) አድዋ ድልድይ ላይ ስለተፈጠረው ሁኔታ በማንሳት ‹‹አሁንም ያንን ድርጊት ፈፅማችሁ ታሳስሩናላችሁ›› ላሉት መናገር የምፈልገው አድዋ ድልድይ ላይ ምን ነበር የተፈጠረው? ፖሊስ ከመረጥነው እና ለከተማ አስተዳደሩ ካሳወቅነው መንገድ ውጪ ያለ ምንም በቂ ምክኒያት እንድንሔድ አስገደደን፡፡ እኛ በፍፁም ይህንን እንደማንቀበል እና የህገወጥ ድርጊት ተባባሪ እንደማንሆን አሳውቅን፡፡ ካሳወቅነው መንገድ ውጪ እንደማንሔድ ባሳወቅንበት ወቅት ፖሊስ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ (የፓርቲውን ሊቀመንበር እስከማነቅ) ሙከራ አደረገ፡፡ በዚህ ያልተደናገጠው ሰላማዊ ሰልፈኛ ለቆመለት አላማ ለመማታት ሳይሆን ለመመታት ዝግጁ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በዚህ ሰዓት ምንም ለማድረግ ህጋዊ ክፍተት ያጡት የፀጥታ ሃይል አዛዦች መንገዱን ለቀቁልን፡፡ በዚህም ተግባራችን መንገዶች እና አደባባዮች የህዝብ የጋራ ንብረት መሆናቸውን አረጋገጥን፡፡
በመጨረሻም እንደሰማያዊ ፓርቲ አባልነቴም ሆነ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰልፉ ላይ የመገኘት መብቴ ለመገደብ የአንድነት ሰልፍ አስተባባሪዎች እና አመራሮች ያደረጉት ድርጊት እጅግ ያስቆጣኝ፣ ያሳዘነኝ እና ያሳፈረኝ ተግባር ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ እንደዚህ አይነት የቆሸሸና ያረጀ አስተሳሰብ ካላቸው አመራሮች እና አባላት እራሱን ሊያፀዳ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ካሆነ አንድነት እንደፓርቲ ይቀጥላል ለማለት አያስደፍረኝም፡፡ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ይዞ ትብብርም ሆነ ውህደት አይታሰብም፡፡ ከታሰበም ከመኢአድ ጋር ተሞክሮ ከጫፍ ደርሷ ተብሎ በመጨረሻ እንደተሰናከለው ከመሆን አይድንም፡፡ አንድነት ውህደት በሚልበት ሰዓት ‹‹መተባበር እንኳ ሳንችል ውህደት ምን ተይዞ?›› ብለን ነበር፡፡ በእሁድ ሰልፉ ላይ ያየሁት ተግባር አንድነት እራሱን ማፅዳት ካቻለ እንኳን ለውህደት ለትብብርም ዝግጁ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡ ባጭሩ እኛ እንደሰማያዊ ፓርቲ አባልነታችን ፓርቲውን ወክለን በቦታው ስንገኝ አንድነት የጠራውን ሰልፍ ደግፈን ለመተባበር ዝግጁ መሆናችንን ለማሳየት ብቻ እና ብቻ ነው፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማበላሸት የሚሞክሩ አመራሮችንም ሆነ አባላትን በማውገዝ አንድነት ፓርቲ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ድርጊቱን የፓርቲው አቋም ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡

ቸር ያገናኘን!!!!

No comments:

Post a Comment