መንግስት ሁል ጊዜም በተደጋጋሚ የሚያነሣው የኢኮኖሚ እድገትን በሚገዳደር ሁኔታ "Ernst
& Young’s attractiveness survey" የሚባል ተቋም በ2013
ሪፖርቱ የለቀቀው መረጃ ባነበብኩበት ሰሞን ማነው ትክክል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ መንግስት የሚያወራውን እድገት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ሁኔታ መረጃዎች ለህትመት ሲቀርቡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡
![]() |
የErnst & Young’s
attractiveness survey የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ
|
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደ ሆነኝ ጉዳይ ስመለስ "Ernst
& Young’s attractiveness survey" የተባለ በአለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚያዊ በተላይም በቀጥተኛ የውጪ ኢንቨስትመንት
(Foreign Direct Investment, FDI) ላይ በሚያደርጋቸው ጥናቶች ታዋቂ የሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሰው ድርጅት ይፋ የሆነው መረጃ ስለ አህጉራችን አፍሪካ መፃኢ እድል ብሩህነት የሚያመላክቱ እጅግ ብዙ መረጃዎችን ይዞ ብቅ ቢልም ስለኛዋ ምስኪን ሃገር የወደፊት እጣ ፈንታ ግን ይዞት የወጣው መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገሮች ተርታ የመግባት እድላችንን ግመልን በመርፌ ቀዳዳ የማሾለክን ያህል የጠበበ መሆኑን ይነግረናል፡፡
ጽሑፉ ስለ አህጉራችን አፍሪካ አገራት የአገር ውስጥ ምርት (GDP) እድገት ትንበያ በሚያወሳበት አምዱ ስር ከ2012-2017 ድረስ ባሉት አመታት ማላዊ 7%፣ ሞዛምቢክ 6.88%፣ ሩዋንዳ 6.5% እና አንጎላ 6.5% የGDP እድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲያደርጋቸው ሃገራችንን በአማካይ በ6.3% የGDP እድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ የአምስተኛነት ደረጃ ይሰጣታል፡፡
መረጃው በ2025 ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ይገባሉ ወይም የመግባት እድል ይኖራቸዋል ብሎ ካስቀመጣቸው አገሮች ተርታ አገራችን ኢትዮጵያ አለመኖሯ ሌላው ለመንግስት አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡ መረጃው እንደሚለው አሁን ባላቸው እድገት ከአፍሪካ ከ10 ያላነሱ አገሮች በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሃገራት ጎራ የመቀላቀል እድላቸው እጅግ የጠበበ ብሎ ካስቀመጣቸው እንደ ኒጀር፣ ላይቤሪያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ እና ሶማሊያን ከመሳሰሉ በእርስ በእርስ ጦርነት ከሚታወቁ ሃገራት ተርታ ሃገራችንን አሰልፏል፡፡ ይህ መረጃ መንግስት ከሚያልመው በአጭር ጊዜ ጎራውን የመቀላቀል ሃሳብ ጋር ፊት ለፊት የሚጋጭ ይሆናል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ብቻ ሳይሆን እየከፋ የሄደው የኑሮ ውድነት ምስጋና ይግባውና ከአፍሪካ የአንደኝነትን ስፍራ የምንይዝበትን ነገር አላሳጣንም፡፡ ጥናታዊ ጽሑፉ ስለ ኑሮ ውድነት ከአለም ባንክ አገኘሁት በሚለው መረጃ የኑሮ ውድነቱን ከ1980-2011 ያለውን እይታ በሰንጠረዥ ሲያስቀምጥ በአፍሪካ በአማካይ የኑሮ ውድነቱ (average
inflation rate of Africa) በ2011
10.1% ሲሆን በሃገራችን ኢትዮጵያ ግን ቁጥሩ 33.2% ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ የሚመጣው ከፍተኛ ኑሮ ውድነት እድገት ማሳያ (Inflation
Growth Rate) የሆነው ቁጥር 18.7% በዩጋንዳ የተመዘገበው ነው፡፡ መረጃው እንደሚለው 1980 በሃገራችን የኑሮ ውድነቱ 4.6% የነበረ ሲሆን ይህም ከአፍሪካ ትንሹ የኑሮ ውድነት ያለባት ሃገር እንደነበረች ያሳያል፡፡
የኑሮ ውድነት ህዝቦች በሃገራቸው የመኖርን ፍላጎት እንዲሁም ለሃገራቸው ያላቸውን ፍቅርም በእጅጉ ይሸረሽራል፡፡ ለዚህም በሃገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የዜጎች አደገኛ እና ህገ ወጥ ስደት ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ህዝቦች በሃገር ውስጥ ሰርተው መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት ጉም የመዝገን ያህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደ እና እየከፋ ሲሄድ በተገኘው መንገድ ከሃገር እና ከቤተሰብ መሰደድን ይመርጣሉ፡፡
ሌላኛው በዚህ መረጃ የተዳሰሰው ደግሞ በአፍሪካ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መዳረሻ ከሆኑ ቀዳሚ 10 ሃገራት ተርታ ሃገራችንም አለመኖሯ ሌላኛው ገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደረጃ በደቡብ አፍሪካ ጀምሮ ናይጄሪያ፣ ግብጽ፣ ዩጋንዳ፣ ኬኒያ፣ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ እና ካሜሩንን ከአህጉሪቷ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መዳረሻ ቀዳሚ ሃገራት ተርታ መሆናቸውን ያትታል፡፡ መንግስት ከአፍሪካ ቀዳሚ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራ ላይ መሆኑን የሚነግረን ከምን ተነስቶ ይሆን? ከላይ ከጠቀስናቸው ሃገሮች የመጨረሻዋ ካሜሩን በ25 የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አከባቢ ኢንቨስት ታደርጋለች፡፡ እኛስ?
ከ2003 ጀምሮ የውጪ ባለሃብቶች ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) መዳረሻ
የሆኑት 10 የአፍሪካ ሃገሮች ደቡብ አፍሪካ (16.5%)፣ ግብጽ (10.5%)፣ ሞሮኮ (10%)፣ ናይጄሪያ (6.2%)፣ ቱኒዚያ (5.9%)፣ አልጄሪያ (5.8%)፣ አንጎላ (5.2%)፣ ኬንያ (4.4%)፣ ጋና (3.7%) እና ታንዛኒያ (2.7%) ናቸው፡፡ እነዚህ ሃገሮች ከአጠቃላይ ወደ አህጉሪቷ የሚመጡ ባለሃቶች 71% መዳረሻ ናቸው፡፡ ጭርሱኑ መረጃው ይግረማችሁ ብሎ ጎረቤታችን ኬኒያን በአፍሪካ ኢንቨስት በማድረግ ቀዳሚ ከሆኑ 10 የአለም አገራት ተርታ አስገብቷታል፡፡ ይህም በኢኮኖሚም ሆነ በዲሞክራሲ ጎረቤቶቻችን ምን ያህል ርቀውን እንደሄዱ ያሳያል፡፡
ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው ተቋም አለም አቀፍ ባለሃብቶች አንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉባቸውን ሃገሮች ተጠይቀው ከተዘረዘሩት 15 የአፍሪካ ሃገራት ተርታ ሃገራችን አለመኖሯ ሌላው አስገራሚ ነገር ሊሆን የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ምክኒያቱም በባለሃቶች ተመራጭ ከሆኑ የአለም ሃገራት ተርታ ተሰልፈናል እያለ የሚደሰኩር መንግስት ከአለም ቀርቶ ከአፍሪካ ሃገራት እንኳን ተመራጭ አለመሆናችን ሲሰማ ከዚህ ሌላ ምን አንገቱን ያስደፋው ይሆን? መንግስታችንስ የውጪ ባለሃብቶችን በመሳብ ተሳክቶልኛል የሚለው ምንን መሰረት አድርጎ ይሆን?
የውጪ ባለሃብትን እና ንብን ለመሳብ ያማረ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ወፍራም ለም መሬት እና ርካሽ የሰው ሃይል ብቻውን ምንም አያደርግም፡፡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቀልጣፋ እና ከሙስና የጸዳ መስተንግዶ እንዲሁም የተረጋጋ ፖለቲካ እና በቂ ዘመናዊ እውቀት ያለው የተማረ የሰው ሃይል ካለ ምንም በሌለበት ምድረ በዳም ቢሆን ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶችን መሳብ
ይቻላል፡፡ የውጪ ባለሃብቶችን ለመሳብ ዋናው ነገር እንደ ባለስልጣኖቻችን ወንበር የተመቸ እንዲሁም እንደ አደይ አበባ ያማረ መስተንግዶ ነው እንጂ ከመንግስት ቀረጥ ወይም ግብር ነፃ እያሉ በየቢሮው ለሚሰበሰብ
"የግለሰቦች ግብር እና ቀረጥ" ወይም ሙስና መዳረግ አይደለም፡፡
ከድህነት ለመውጣት የመጀመሪያው ተግባር መሆን ያለበት የድህነታችንን ደረጃ እና አስከፊነት አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የድህነታችን አስከፊነት ከመቀበል ይልቅ መንግስት በሃገሪቷ ላይ ያለውን ድህነት ለመሸፋፈን ስለ ባለሁለት አሃዙ እድገት ማውራትን ትቶ ህዝብን ያሳተፈ ስር-ነቀል መፍትሄ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱ የአብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚነት ያላረጋገጠ በመሆኑ በህገ-ወጥ መንገድ ከሃገራቸው በመሰደድ ላይ ያሉትን ወጣቶች መገደብ አለመቻሉ እና አደገኛው ህገ-ወጥ ስደት ተባብሶ መቀጠሉ ለመረጃው እውነተኛነት ማረጋገጫ ነው፡፡
በመጨረሻም ተማረ የምንለው የህብረተሰባችን ክፍል በስራ ማጣት በሚሰቃይበት ሁኔታ ስለ ኢንቨስትመንት ማውራት፣ መጨረሻው ኮብልስቶን እንደሆነ እያሰበ ትምህርቱን የሚከታተል ወጣት ባለበት ሃገር ስለ ትምህርት ጥራት መለፈፍ፣ አብዛኛው ህዝባችን በቀን ሁለቴ ተመግቦ ማደር የቅንጦት ያህል እየከበደው ስለ ፈጣን እድገት ፕሮፖጋንዳ መንዛት፣ አብዛኛው የገጠሩ ህዝብ ለመጠጥ የተበከለ የወንዝ ውሃ ከመቅዳት ሳይላቀቅ ስለ መሰረተ ልማት መስፋፋት መደስኮር እንዲሁም ግብርናው የሰው ልጅ ማረስ እንደጀመረበት ወቅት በበሬ ከማረስ እና ዝናብ ከመጠበቅ ሳንላቀቅ ስለ መካናይዝድ ግብርና መለፈፍ መራር እና ገዳይ ቀልድ ነው፡፡ ድህነት እንደኮሶ የተጣባን ችግሩን ከመሰረቱ ከመቅረፍ ይልቅ በማለባበስ ላይ በማተኮራችን ነው፡፡ ድህነት በዘር የሚተላለፍ በሽታ አይደለም፡፡ አንድ ቀን በሃገራችን መልካም አስተዳደር እና ዲሞክራሲ ሲሰፍን እንዲሁም የሰብዓሰዊ መብት ሲከበር እንደ አሮጌ ጫማ አውጥተን ልንጥለው የምንችልለው ጉዳይ ነው፡፡
ችግርን ከማዳፈን ይልቅ በማጥፋት ላይ እናተኩር!!
No comments:
Post a Comment