Saturday, 15 March 2014

‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና››




እምባ እምባ ይለኛል፤
ይተናነቀኛል
ግን እምባ ከየት አባቱ፤
ደርቋል ከረጢቱ፡፡
ሳቅ ሳቅም ይለኛል፤
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እያለቀሰች
      መከረኛ ነፍሴ፡፡

በዓሉ ግርማ ‹‹ኦሮማይን›› ሲፅፍ ምን ተሰምቶት ይሆን ይህንን ግጥም የፃፈው? ለካስ እውነትም መከፋት እንደዚህ ነው፡፡ እምባም ሳቅም ሲጠፋ እንደዚህ ነው፡፡ ሳቃችንንም እምባችንንም ያለጊዜው ጨርሰን ባዶዋችንን ቀርተናል፡፡ ለነገሩ ከዚህ አስከፊ ስርዓት ውጪ የማናውቅ የዚህ ዘመን ልጆች ገና ስንወለድ ማልቀስ የጀመርን ይኸው እስከ አሁን ድረስ እምባችንን በሳቅ፤ ሃዘናችንን በደስታ የሚቀይር ስርዓት ሳይፈጠር የመከራ ኑሮን እንገፋለን፡፡
አሁንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ድምፃችንን ከማሰማት ወደ ኋላ አንልም፡፡ ይህ ስርዓት እስካልተወገደ ድረስ እረፍት የሚባል ነገር አይኖረንም፡፡ በእስራታችን ብቻ ሳይሆን ደማችንንም አፍሰን ሆነ ውድ ህይወታችንን ገብረን ኢትዮጵያዊ ክብራችንን እናስመልሳለን፡፡

‹‹የጣይቱ ልጅ ነኝ›› ወይም ‹‹የምኒሊክ ልጅ ነኝ›› ማለት የሚሳስር ብቻ ሳይሆን የሚያስገድልም ከሆነ አሁንም  በሃፍረት አንገታችሁ ተሰብሮ ጉልበታችሁን እስኪነካ ድረስ ደግሜ ደጋግሜ እንላለው ‹‹የጣይቱ ልጆች ነን›› ‹‹የምኒሊክ ልጆች ነን››፡፡ እርርርርርርርርርርርረ በሉ!!!! ብችልማ አድዋ ተራራ ላይ ቆሜ ነጋሪት እያስጎሰምን ነበር ማወጅ የነበረብኝ፡፡ እንዴት የአድዋውን ጌታ እና የአድዋዋን እመቤት ስም አታንሱ ትላላችሁ? አድዋ እኮ ማንነቴ ነው፡፡ አድዋ እኮ የኢትዮጵያዊነቴ እና የጀግንነቴ ህያው ምስክር ነው፡፡ አድዋን ያለ ምኒልክ፣ ያለ ጣይቱ፣ ያለ አሉላ፣ ያለ ባልቻ፣ ያለ አውአሎም…እንዴት አድርጌ ላስባት፡፡ አንድ ላይ የተሰፉ የአንድ ሳንቲም አንድ ገፅታዎች እኮ ናቸው፡፡ ለነገሩ እናንተ የማን ልጅ ሆናችሁ?

ጣሊያንን ባንዲራ እያውለበለበ የተቀበለ፣ መንገድ የመራና ፓስታ ቀቃይ የነበረ ማንነታችሁን አሁንም አለቀቃችሁም፡፡ ባንዳነት በዘር የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ ስላሳወቃችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ለነገሩ ባንዳነት በሁለት ይከፈላል፡፡

የመጀመሪያው ለሆዱ ያደረ ባንዳ ነው፡፡ የዚህ ባንዳ መገለጫው የግል ጥቅሙ ከተጠበቀለት እና ሆዱ ከተሞላበት ስለተቀረው ነገር ደንታ የለውም፡፡ ‹‹ሆድ ከሃገር ይሰፋል›› የሚለውን ብሂል በተሳሳተ መንገድ የገባው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ አይነቱ ባንዳ በቁርጥ ቀን ለሃገራቸው ውለታ ውለው ባንድነታቸውን እንደኩፍኝ አራግፈዋል፡፡ ምሳሌ አውአሎም መውሰድ እንችላለን፡፡ በቁርጥ ቀን ባራቴሪን የጋለ ብረት ምጣድ ላይ ጥደውት ‹‹እስሀ ዝዋአልካዩ አያውለና (ውሎህን አያውለኝ)›› ያሉ ጀግና ናቸው፡፡

ሁለተኛው የባንዳ አይነት ሆዱን ብቻ ሳይሆን ህሊናውም ሳይቀር አሽከር ያደረገ ባንዳ ነው፡፡ የረባ ምግብ እንኳን ሳይሰጣቸው በትርፍራፊ ሃገር ሲያስፈጁ የነበሩ ባንዶች ናቸው፡፡ ነጭ አምላካችን ነው ብለው ያመልኩ የነበሩ ባንዶች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ባንዶች እጅግ አሳፋሪው ድርጊታቸው ሚስታቸውን ሳይቀር ያላወቁ በመምሰል ለነጭ ያስተኙ የነበሩ ናቸው፡፡ ሚስታቸው ከነጭ አርግዛ ነጭ ልጅ ስትወልድላቸው ለአሳዳሪያቸው ‹‹ፈጣሪ ለእርሶ ያለኝን ፍቅር አይቶ ነጭ ልጅ ሰጠኝ፡፡›› የሚሉ ናቸው፡፡

ታዲያ አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ከነጩ ልጅ ወገን ይሆኑ እንዴ?

ለማንኛውም ለጠቅላላ እውቀት ብዬ ቀንጭቤ አነሳሁት እንጂ ወደፊት በሰፊው ስለምመለስበት ለአሁኑ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ የጣይቱ ወይም የምኒልክ ልጆች አይደላችሁም ለሚሉን ሰዎች የተወዳጁን ‹‹የኛና›› የሙዚቃ ቡድንን አባላትን ይጠይቅ፡፡ ‹‹እቴጌይቱ››ን ዘፈን በሚያምረው ህብረታቸው
‹‹የጀግናዋ ልጅ ነኝ የጣይቱ ፍሬ፤
የቁርጥ ቀን ብልሃት እኔም አለኝ ዛሬ፡፡
መች ፈሪ ነኝና ወደኋላ እላለሁ፤
ካሰብኩት ደርሳለሁ ታላቅ እሆናለሁ፡፡
ዘራፍ!! ዘራፍ!!…
ምያለሁ በጀግናዋ እናቴ፤
ውርድ ከራሴ ለዚያ ጠላቴ፡፡
ወድቆ ሳላየው አንላቀቅም፤
የምን ፍራቻ ታሪክ ሳልደግም፡፡
ጣይቱ ማለት እኔ ነኝ ዛሬ፤
አለሁልሽ ባይ ለእናት ሃገሬ፡፡
ባለመፍትሄ የስኬት አንጋሽ
ያን ጀግንነቷን እኔ ነኝ ወራሽ፡፡›› በማለት በሚያምረው ድምፃቸው ያዜሙለታል፡፡
እኛም ይህ አምባገነን የታሪክ ነቀዝ መንግስት ወድቆ ሳናየው አንላቀቅም፡፡ ምንም ፍራቻ ይሉት ነገር የለም፡፡ የማን ልጅ ሆነን እንፈራለን? የዩሃንስ፣ የቴድሮስ፣ የምኒልክ፣ የጣይቱ፣ የአሉላ፣ የባልቻ፣…ልጆች ሆነን እንዴት እንፈራለን?

‹‹የበላይ ልጅ ነኝ›› ማለት የሚያሳስር ከሆነ አሁንም እንደግመዋለው ‹‹የበላይ ልጅ ነኝ››፡፡ ከፈለጋችሁ የተወዳጁን የባህል ሙዚቀኛ አሸብርን ዘፈን የማያሸብራችሁ ከሆነ አድምጡት፡፡ እኔ ልጀምርላችሁ…
      ‹‹የበላይ ልጅ ነኝ የዛ ሳተና
       የስመ ጥሩ ቆራጡ ጀግና…››

ሞትን ያክል ነገር ከቁም ነገር የማይጥፈው የባንዳ እና ወራሪ የእግር እሳት የነበረው የበላይ ዘለቀ ልጆች ሆነን ፍርሃትን ምን አመጣው? ምን እንዳንሆንስ እንፈራለን? ምን ስላለን እንፈራለን? ምንም የሌለው ምንም አይፈራም፡፡ ፈሪነት የባንዳ ልጆች እንዲሁም ጀግንነት የአርበኛ ልጆች መገለጫ ነው፡፡
በመጨረሻም እቺን ግጥም ጣል አድርጌ ልሰናበት!!
           
            ‹‹የጣይቱ የልጅ ልጅ›› የጠላት መርዶ የብዕር ልሳኔ ይናገር
እንኳን ለእስራት ይቅርና ለሞት ከቶም አልደነብር፡፡
አዎ፡- እኔ እንደሁ ጥንትም አውቃለሁ
አያቴ በንጉስ ጭራ ቆይ፤ በባሩድ ማረር መክሰሉን
በእርሳስ መለብለብ መንደዱን
እናም አሁን ‹‹የበላይ ዘለቀ ልጅ››  እስራትን አይፈራም በለው፡፡
ለአደግዳጊ ቧልተኛ ለእንከፍ አሳባቂ ይብላኝ እንጂ
እስራት እንደሁ አብሮኝ የኖረ ስቅላትም ያባቴ ነው፡፡
ግን አንቺ ጥቁር አገር---ጥቁር አፈር
መፀነሻ ከርስ የጥቁር ዘር
አያልፉሽ ጋራሽ ይናገር
አባይ ጅረትሽ ይመስክር
ላንቺ የኖረ ማን ሆኖ?
ላንቺ የሞተ ማን ሆኖ? ባንቺስ የኖረ ማን ነበር?


























No comments:

Post a Comment