Saturday, 22 March 2014

የሰማያዊ ትውስታዬ



ሰሞኑን በግል ጉዳይ ምክኒያት ከተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተቆጥቤ አብዛኛውን ጊዜን ከቤተሰብ እና ከቅርብ ዘመዶቼ ጋር የማሳለፍ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከቤተሰቦቼ በተለይም ከእናት እና አባቴ ጋር ስለ ፖለቲካ ሕይወቴ በሰፊው እና በግልፅነት የማውራት እድሉ ገጥሞኛል፡፡ ይህንን ስል ከዚህ በፊት ከቤተሰቦቼ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ አላወራም ነበር ማለት መስሏችሁ የተረዳችሁ ካላችሁ ፈጽሞ ተሳስታችኋል፡፡ ፍፁም ከቤተሰቤ የተደበቀ ህይወት የለኝም፡፡ እያንዳንዷን ነገር ላይ የጥንቃቄ ምክራቸውን አይነፍጉኝም፡፡ እያንዳንዷን እርምጃዬን በጥንቃቄ አደርግ ዘንድ የዘወትር ምክራቸው ነው፡፡ እዚህ ጋር ቤተሰቦቼ እኔ ያለሁበትን የፖለቲካ አመለካከት ከልባቸው ደፍሬ ይደግፋሉ ማለት ባልችልም እኔን የሚያስደስተኝ ነገር ሁሉ እንደሚያስደስታቸው በሚገባ ስለማውቅ አሁን ባለሁበት የፖለቲካ ተሳትፎ ደስተኛ ናቸው ለማለት እደፍራለሁ፡፡
አንድ ቀን ጠዋት እናቴ አዳሬን ለማየት ወደተኛሁበት ክፍል መጣች፡፡ ወደ ክፍሉ ስትገባ እኔ እና አባቴ ክፍሉ ውስጥ ነበርን፡፡ አባቴ የተለመደ ምክሩን እየሰጠኝ ነበር፡፡
‹‹ልጄ›› ብሎ ነበር የጀመረው፡፡ ‹‹ልጄ ስለ እውነት ኖረክ ስለ እውነት ብቻ ሙት፡፡ እኔ ስለ እውነት ብለህ፣ ስለዚች ሃገር ክብር እና ስለህዝቧ ፍቅር ስትል በምታደርገው ትግል ውስጥ ብትታሰር ወይም የአካል ወይም የህይወት መሰዋዕት ብትሆን የኩራት እንባ አነባ እንደሆን እንጂ አንድም ሃዘን አይሰማኝም፡፡ የመረጥከው መንገድ ትክክልም ይሁን አይሁን ሁል ጊዜም ለመረጥከው መንገድ ወይም ለእውነትክ መሰዋዕት ለመሆን ወደኋላ እንዳትል፡፡ ልጄ ጀግንነት ለቆሙለት አላማ አስፈላጊውን መሰዋትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን ብቻ ሳይሆን መክፈልም ጭምር ማለት ነው፡፡ በህይወት ቆይታህ ስለህዝብ ፍቅር፣ ስለሃገር ክብር እና ነፃነት መሞት ከመኖር የተሻለ መኖር ነው፡፡ በሰዎች ልብ ውስጥ ነግሰህ ትኖራለህ፡፡ ነገር ግን የውሸት ኖረክ ስለ ሆድክ አድረክ የሞትክ ቀን ዳግም ሞት ትሞታለህ፡፡ ስለ ውሸት መኖር እና ስለሆድክ ማደር የጀመርክ ቀን በሰዎች ልብ ውስጥ ትሞታለህ፡፡ ልጄ አካላዊ ሞት ከመሞትህ በፊት እንዳትሞት ተጠንቀቅ፡፡ ድሮ ኢህዴጎች ጫካ ሲገቡ የትግሬ እናት ልጇን ምን ብላ እንደመረቀች ታውቃለህ? "ጥይት ጀርባህን እንዳይመታህ" ነበር ያለችው፡፡ ይህንን ስትል ማስተላለፍ የፈለገችው ነገር ለጥይት ግንባርህን ስጥ እንጂ ስትሸሽ ጀርባህ ተመትተህ እንዳትሞት ማለቷ ነበር፡፡ አንተም ዛሬ የምመክርህ ነገር ስለእውነትህ ከሆነ ግንባርህን ሳታጥፍ ግንባርህን ለጥይት ወይም አንገትህን ለገመድ ስጥ›› እያለ ምክሩን ሲለግሰኝ ሁለታችንም የእናቴን ወደ ክፍሉ መግባት አላስተዋልንም ነበር፡፡
‹‹ሁሉም ነገር እውነት ነው›› በማለት ንግግሯን ጀመረች፡፡ ቀጥላም ‹‹ምክርህ ሁሉ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የትግሬዋን እናት ምክር የተረጎማችሁበት መንገድ ትክክል አይመስለኝም፡፡ የልጇን ጀግንነት እና ፈሪነት ከእናት በላይ ማን ያውቃል? የትግሬው ታጋይ እናት ልጇ ፈሪ እንዳልሆነ በሚገባ ታውቅ ነበር፡፡ ጥይት ጀርባህን እንዳይመታህ ስትል አትሽሽ ማለቷ አልነበረም፡፡ ልጇ እንደማይሸሽማ ታውቃለች፡፡ መቼም የጥይት መዓት ወደሚበተንበት ጫካ የሚሄደው ልጇ የደርግ ወታደር ፈንዲሻ እየበተነ ይቀበለኛል ብሎ እንደማያስብ ታውቃለች፡፡ ያቺ እናት ጥይት በሚያውካካበት ግንባር የከበሮ ድምድምታ የሚጠብቅ ልጅ ወልዳ እንዳላሳደገች ታውቃለች፡፡ የትግሬ እናት እንደዚያ ብላ የመረቀችው አብረውክ ጫካ የሚገቡትን ሰዎች ተጠንቀቅ ማለቷ ነው፡፡ ከኋላ በጥይት እንዳትመታ ማለቷ ነበር፡፡ አንተ ሃገር እና ወገን ብለህ ግንባርህን ለጥይት ስትሰጥ ስልጣን እና ሃብት ብሎ ጫካ ከገባ ሰው ጀርባህን ጠብቅ ማለቷ ነበር፡፡ እኔም ዛሬ አንተን የምልህ ስለእውነት ግንባርህን እንደማታጥፍ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ እውነትክን ለመከላከል አባትህ እንዳለው ግንባርህ ለጥይት እና አንገትህን ለገመድ እንደምትሰጥ አልጠራጠርም፡፡ ልጄ እውነትህ ሃገርህ ናት፡፡ እውነትህ ወገንህ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ እውነት የለህም፡፡ በአንተ እና በመሰሎችህ እውነት ተከልለው የውሸትና የጥፋት ተልዕኮ ከሚያራምዱ ሰዎች ጀርባህን ጠብቅ፡፡ ልጄ ለሚያምኑበት ሰው ነው ጀርባ የሚሰጠው…፡፡ በዚህ ወቅት ለመሞት እንጂ ለመግደል ጫካ እንድትገባ እና ከወንድሞችና እህቶችህ ደም እንድትቃባ አልመክርህም፡፡ ልጄ ሃገር በደም አትገነባም፡፡ ሰው ለማኖር ሰው ይሞታል እንጂ ሰው አይገደልም፡፡ በአለም ላይ በመሞቱ እንጂ በመግደሉ ሰው ያኖረ ጀግና የለም፡፡ ሙት እንጂ አትግደል፡፡ እውነተኛ ታጋይ ከሆንክ የትግል አጋሮችህን ስቃይ አንተ ለመሰቃየት እንዲሁም ሞታቸውን ለመሞት እራስህን ቅድሚያ አዘጋጅ፡፡ ጀግና ሰው ለመሰዋዕትነት ይሽቀዳደማል›› ብላ አባቴን አስከትላ ወጣች፡፡
ከዚያ በኋላ የቤተሰቦቼን ምክር አሰላሰልኩት፡፡ በተለይም ‹‹ለሚያምኑበት ሰው ነው ጀርባ የሚሰጠው›› የሚለውን የእናቴን ምክር አሰብኩት፡፡ እውነት ነው፡፡ ግንባርን በአይን ጀርባን በወዳጅ ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
ከዚያማ አብረውኝ የምታገላውን የትግል ጓዶቼን አሰብኩ፡፡ በሃሳብ እሁድ ማርች 9/ 2014 መገናኛ አደባባይ የሴት የትግል አጋሮቼን የነፃነት ሩጫ ለመታደም ከወንድ ጓዶች ጋር ታድሜ ነበር፡፡ በመነሻው አከባቢ ስለነበርን ሩጫውን እየተከታተለ መረጃዎችን እንዲያደርስ ከተመደበው ቡድን ጋር በስልክ ሁሉም ነገር መልካም እና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተካሄደ እንዳለ በመስማታችን ሁላችንም ፊት ላይ የደስታ ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ትንሽ በአከባቢው ዞር ዞር ብለን ሴቶቻችን ሩጫው መጠናቀቂያ አከባቢ እየደረሱ መሆኑን ስለተነገረን ወደ አከባቢው ተመለስን፡፡ ከጥቂት ጉጉት በኋላ ጀግኖቻችን ቦታቸው ላይ ደረሱ፡፡ ሁላችንም እጃችንን በማውለብለብ በሰላም በመምጣታቸው እንዲሁም ሃሳባቸውን በነፃነት በማንጸባረቃቸው ደስታችንን እና ድጋፋችንን ገለጥንላቸው፡፡
ነገር ግን ሴት ጀግኖቻችንን የተቀበላቸው የእኛ እቅፍ ሳይሆን የፖሊስ እጅ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን እንደሚችል የገመትነው ነገር ቢሆንም ጀግኖቻችንን አቅፈን ደግፈን ለመቀበል የነበርን ጉጉት በአጭሩ በመቀጨቱ ነው መሰል ሁላችንም ፊት ላይ የነበረው ቁጣ እና ሃዘን ለመግለጽ ይከብድ ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ሁላችንም ከፖሊሶቹ ጋር ብንተናነቅ ደስ ባለን ነበር፡፡ ግን ያንን ማድረግ ከትርፉ ኪሳራው ስለሚያመዝን ሁለቱ ጀግኖች (ብርሃኑ እና ጌታነህ) ፖሊሶቹን ሴቶቹ ለምን እንደተያዙ ለመጠየቅ ተለይተውን ሄዱ፡፡ እኛ ባለንበት ቦታ ሆነን ሁኔታውን በአንክሮ መከታተላችንን ቀጠልን፡፡ ፖሊስ ለቀረበለት ተገቢ ጥያቄ የሰጠው መልስ ወንዶቹን በአባሪ ተባባሪነት ከሴት ጀግኖቻችን ጋር መቀየጥ ነበር፡፡ ከዚያም ከእኛ ጋር የነበረው ጀግናው ወጣት አቤል የሴቶቹን ጀግኖች ስልክ በአንድ ቦርሳ ውስጥ ሰብስቦ ይዞ ስለነበር በፖሊሶች እይታ ስር ወደቀ፡፡ በቁጥጥር ስርም አዋሉት፡፡ በዚህ ወቅት ፊቱ ላይ ይነበብ የነበረው ጀግንነት እና የአላማ ጽናት በቃላት መግለጥ ከምችለው በላይ ነው፡፡
እዚህ ጋር ‹‹እውነተኛ ታጋይ ከሆንክ የትግል አጋሮችህን ስቃይ ቅድሚያ አንተ ለመሰቃየት እንዲሁም ሞታቸውን ቅድሚያ ለመሞት እራስህን አዘጋጅ›› የሚለውን የእናቴን ምክር አስታወሰኝ፡፡ እነዚህ ጀግኖች ስቃዬ ለመሰቃየት እንዲሁም እስራቴን ለመታሰር እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ እውነተኛ ታጋዮች ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የጣይቱ ልጆች ስለሆኑት ሴት ጀግኖች ስናወራ ወንዶችን አናብስት እንዳንረሳ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ከእነዚህ አናብስት ጋር የተገናኘነው ከፍርድ ቤት ተመልሰው በእስር ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ሳይባቸው የነበረው በራስ መተማመን እና ጀግንነት አንዳችም ሳይቀንስ እንዲያውም ጨምሮ ነበር፡፡ ያ የመጨረሻ አካላዊ ትውስታዬ ነው፡፡ በምናብ ግን ሁሌም አብሬያቸው ነኝ!!
በመጨረሻም፤ እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ስቃዬን ለመሰቃየት፣ እስራቴን ለመታሰር እንዲሁም ሞቴን ለመሞት የተዘጋጁ እውነተኛ ታጋዮች ያሉበት ሰማያዊ ቤት ገብቻለሁ፡፡ አሁንስ ‹‹ጀርባዬን ለማን እሰጣለሁ?›› ብዬ አልጨነቅም፡፡ ከጀርባቸው በላይ ጀርባዬን የሚጠብቁልኝ ጀግና የትግል አጋሮች አሉኝ፡፡ ‹‹ጀርባ ለወዳጅ ነው የሚሰጠው›› ነው ያልሽው እማሚ? እውነት ነው፡፡ ቢያንስ ጀርባዬን መከራ እንደማያገኘው አረጋግጫለሁ፡፡ እውነተኛ የትግል ስልት እና እውነተኛ ታጋዮች ይዤ ለምን እፈራለሁ፡፡ እውነትን ይዤ በሞት ጨለማ ውስጥ እንኳ ብሔድ አልፈራም!! አባቢ እውነትህን ነው ስለእውነት፣ ስለሃገር፣ ስለወገን ነፃነት ግንባሩን ለጥይት እንዲሁም አንገቱን ለገመድ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ አድርገህ አሳደከኝ እንጂ ፈሪ አላደረከኝም፡፡ ክብር እና ምስጋና ለእናንተ ይሁን!!!
ፍቅር፣ ብርታቱን እና አንድነቱን አይንፈገን!!
የነገ ሰው ይበለን!!            

No comments:

Post a Comment