የተለያዩ ሚዲያዎች እንደምንሰማው ሀገራችን ኢትዮጵያ በአለማችን እጅግ ፈጣን እድገት
(growth) ከሚያስመዘግቡ ሃገሮች አንዷ እንደሆነች ይነገራል፡፡ በአንድ አገር እድገት አለ ለማለት መለኪያው የህዝብ ተጠቃሚነት
ነው፡፡ ታዲያ ህዝቡ ከዚህ እድገት ምን አተረፈ?
የመንገድ፣ የት/ት ተቋማት፣ የጤና ማዕከላት … እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ
መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሚስራባቸው ፕሮጀክቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ምን ያህል ጥራትን መሰረት ያደረጉ ናቸው?
አንዳንዶች ጥራት ቀስ በቀስ ይመጣል ሊሉ ይችላሉ፡፡ በእኔ እምነት ግን ከብዛት ጥራት ያሳስበኛል፡፡
አንድ አዲስ ዩኒቨርሲቲ ወይም ሆስፒታል ከመገንባት የነባሮቹን አቅም መገንባት የተሻለ ነው፡፡ የበግ መንጋ ውስጥ እንደገባ ተኩላ
ማህበረሰቡን የሚያምሰው ከነዚህ ጥራት የሌላቸው ትምህርት ተቋማት የሚመረቀው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ከግብርና ትምህርት ተቋሞቻችን
የምናስመርቃቸው ባለሞያዎቻችን ጥራት ከሌላቸው በዘርፉ የሚተዳደረውን ህብረተሰብ ክፍል ወዳልተፈለገ መንገድ እየመሩ እንኳን ለተቀረው
ህብረተሰብ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጥ እራሱንም መመገብ ይሳነዋል፡፡ እንዲሁም ጥራት የሌለው የጤና ባለሙያ እንኳንስ ህብረተሰብን
ከበሸታ ሊጠብቅ እና ሊፈውስ እራሱም መገኛው ከሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ይልቅ በየ መጠጥ እና ጫት ቤቱ ይሆናል፡፡
በጤናው፣ በቤቶች ልማት እና በመንገዱ ዘርፍ የምናካሂዳቸው ግንባታዎች ይበል የሚሰኙ ቢሆኑም የእነርሱም
የጥራት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የመንገዱ ግንባታ ከምጠናቀቁ በፊት ከመጀመሪው የሚፈረካከስበት ሁኔታ ትንሸ አይደለም፡፡ በግንባታ
ስም ነባር መንገዶች ተቆፍረው ለአመታት ህዝብን ለተለያዩ ችግሮች ማጋልጣቸው በየአከባቢው የተለመደ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም በጋራ መኖሪያ
ቤቶቻችን አከባቢ የምናየው የጥራት እና ተያያዥ ችግሮች ለግንባታ ካወጣነው ወጪ በላይ እያስወጡን ይገኛሉ፡፡ ቤት ገንብቶ እና የጤና
ጣቢያ ወይም ሆስፒታል የሚል ታፔላ ለጥፎ ጤና ጣቢያ ወይም ሆስፒታል ማለት አይቻልም፡፡ ጤና ተቋማትን ጤና ተቋማት የሚያሰኛቸው
የተለጠፈባቸው ታፔላ ሳይሆን የሚሰጡት አገልግሎት ነው፡፡ ቀላል የመመርመሪያ መሳሪያዎች እንኳን በሌለበት የጤና አገልግሎት ተስፋፍቷል
ማለት እራስን ከማታለል ተለይቶ አይታይም፡፡
በውሃ፣ ስልክ እና መብራት በኩልም ያለው የጥራት ችግር ከላይ ከተጠቀሱት የሚለይ ጉዳይ አይደልም፡፡
የአገሪቷ ብሎም የአህጉሪቷ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ እንኳን የነዚህ መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡
ያልተቆራረጠ የንጹህ ውሃ፣ የስልክ እና የመብራት አገልግሎት ተደራሸነት ምን ያህል ነው? የተዘረጋው ኔትዎርክ መሸከም ከሚችለው
በላይ የስልክ መስመሮችን በመሸጥ ዘርፉ አድጓል ማለት ምን ያህል ተገቢ ነው? የሚሉ እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ማግኘት
ከቻሉ እድገታችን ወዴት እና እንዴት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡
በእኔ እምነት ከመሰረተ ልማት ባልተናነሰ መልኩ የእድገት መለኪው የህዝባችን የኑሮ ሁኔታ ምን ያህል
ተለውጡዋል የሚለው መታየት አለበት፡፡ እውነቱን ለመናገር የህዝባችን የኑሮ ሁኔታ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ድሮ ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ
የማያሳስበው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ቤት እና ልብስ የቅንጦት እየሆኑ የምግብ ፍላጎቱን እንኳን በዝቅተኛ ሁኔታ ማሟላት ተስስኖታል፡፡
85% ነው የሚባለው ገበሬው ሕዝባችን እንኳን እራሱን መመገብ ተስኖታል፡፡ ይህ ገበሬ አሁንም ከዝናብ ጠባቂነት እና ከኋላቀር አስተራረስ
ዘዴ ሊወጣ አልቻለም፡፡
ለግብርና የተመቸ መልከዓ ምድር እና ለም አፈር እንዲሁም ለመስኖ የሚውሉ በቂ ወንዞች ያሏት አገር
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በሚሄድ በምግብ እራስን ያለመቻል ችግር ውስጥ ስትዳክር አለም በአግራሞት እየተመለከታት ይገኛል፡፡ ታዲያ
ይህንን ኋላቀር የሆነ የግብርና ስርዓት ካለበት ችግር ቀና ማድረግ ካልተቻለ እድገቱ ምኑ ላይ ነው? ያለንን ለም መሬቶች ከገበሬው
እየነጠቅን ገበሬውን ከቀዬው እያፈናቀልን የምናስመዘግበው እድገት ምን ያህል ሕዝባችንን ተጠቃሚ ያደርገዋል?
በእኔ አመለካከት የአንድ አገር እድገት በገነባችው መሰረተ ልማት ከሚገለጸው በላይ በእጅጉ ራስን
በመቻል ይገለጻል፡፡ ምን ያህሉ ህዝባችን በምግብ እራሱን ቻለ? ከውጪ መንግስታት የምናገኘው የምግብ እና የገንዘብ እርዳታ በምን
ያህል ቀነሰ? ከዚህ ቀደም የወሰድናቸው ብድሮችን የመክፈል አቅማችን በምን ያህል ጨመረ? እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ካለፉት የሃገሪቱ
መንግስታት ጋር ብቻ ሳይሆን ቀድሞ በድህነት ሰንጠረዥ ውስጥ አብሮ ስማችን ሲፃፍልን ከነበሩ የአፍሪካ፣ የኤሲያ፣ የአውሮፓ እና
የአሜሪካ አገሮች ጋር እራሳችንን ማወዳደር ይጠበቅብናል፡፡
እድገታችን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ካስፈለገ በሌሎች አገሮች ችሮታ ለይ የተመሰረተውን የምግብ
ዋስትናችንን በበቂ ሁኔታ መመለስ እና ማረጋገጥ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ አበባ ወይም የኤሌክትሪክ ሀይል ሸጦ
በሚገኝ የውጪ ምንዛሪ ስንዴ እና ሩዝ እየገዙ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሙከራን ነዳጅ ሸጠው ስንዴ እና ሩዝ በመግዛት የህዝባቸውን
የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ለሚሞክሩ የአረብ አገራት ትተን በቀጥታ በአገራችን ምርት የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ መስራት ይኖርብናል፡፡
አለበለዚያ ግን በአገራችን ላለው የዋጋ ንረት የአለም አቀፉን የምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረከተ የሚለው
አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት ሁልጊዜ መስማታችን አይቀሬ ነው፡፡
ወደ ውጪ ከምንልካቸው ምርቶች (export commodities) በላይ ሊያሳስበን የሚገባው ነገር
ከውጪ የምናስገባቸውን ነገሮች (import commodities) በሃገር ውስጥ ለመተካት (import substitution) የምናደርገው
ጥረት ነው፡፡ የውጪ ምንዛሪ (foreign currency) ለማግኘት እያልን ከምንልከው ቆዳ ያገኘነውን የውጪ ምንዛሪ መልሰን ከቡና
ያገኘነውን የውጪ ምንዛሪ ጨምረን ጫማ እና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን የምንገዛበት ከሆነ እንዲሁም ከአበባ እና የቅባት እህሎች ያገኘነውን
የውጪ ምንዛሪ መልሰን ለስንዴ እና ዘይት የምናውጣው ከሆነ መቼም ከውጪ ምንዛሪ አዙሪት አንወጣም፡፡ ሁል ጊዜም በሃገራችን ምርት
ፍላጎታችንን ለማሟላት የምናደርገው ጥረት ወደ ትክክለኛ የእድገት መንገድ ያደርሰናል ንገረ ግን የህዝባችንን ፍላጎት
(domestic demand) ሳናሟላ ወደ ውጪ ከምንልካቸው ምርቶች የምናገኘውን የውጪ ምንዛሪ መልሰን ያጎደልናትን የህዝብ ፍላጎት
(demand and supply gap) ለመሙላት ተጨማሪ የውጪ ምንዛሪ ይዛብን ትሄዳለች፡፡ ስንዴ ሸጦ ስንዴ ወይም ዱቄት ከመግዛት
ስርዓት መውጣት ይኖርብናል፡፡ ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት እንኳን ይህንን ለማሟላት ቢሞከር ኖሮ የህዝባችንን የምግብ ጥያቄ በሌሎች
አገሮች መልካም ፈቃድ ላይ ተንጠልጥሎ ባልቀረ ነበር፡፡ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ጉዳይ የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎቶች
ከማንም ጥገኝነት ነጻ በሆነ መልኩ ማሟላት ነው፡፡ የዚህን ታላቅ እና ኩሩ ህዝብ ታላቅነት እና ኩራት መመለስ ከፈለግን ከአሳፋሪው
የምግብ ልመና መላቀቅ ይኖርብናል፡፡
ሌላው የእድገታችን ትሩፋት መሆን የነበረበት እና ሳይሆን የቀረው ከሃገሪቷ በተለያዩ መንገዶች የሚሰደደው
ህዝቧ መቀነስ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች የሚሰደደው ህዝባችን ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ ይህ የሚታይ
እውነታ ስለሆነ እድገቱ የህዝብን ተጠቃሚነት አላረጋገጠም ለማለት እንደ አንድ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡ ሕዝባችን በእቃ መጫኛ ኮንቴነሮች
ሳይቀር በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ለመጓዝ የሚያደርገው ሙከራ ምክንያት የባዕድ አገር ናፍቆት ይሆን? ለመሰደድ በሚሞክሩበት ወቅት
በኮንቴነር ታፍኖ፣ በበረሀ ሃሩርና ውሃ ጥም ተቃጥሎ፣ በባህር ሰጥሞ እንዲሁም በድንበር ጠባቂዎች ተደብድቦ እና ተሰቃይቶ መሞት
የተለመደ ቢሆንም ሕዝባችን ግን አሁን ካለበት አሰቃቂ ድህነት ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ ስደት ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
በስደት የሞተ ጎረቤቱን ሰልስት እንኳ ሳይደርስ ለስደት ሻንጣውን የሚሸክፍበት አገር አለች ከተባለ የኛው አገር እማማ ኢትዮጵያ
የመሆን እድሏ ሰፊ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን እና ሊቢያ በረሃ አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት የሚጓዘው የተማረው የሃገሬ
ሰው በሃገሩ ስርቶ ድህነትን በእውቀት ጥይት ማንበርከክ ቢያቅተው እና የቤተሰብ ድህነት ቢያንገበግበው አውሮፓ ተስፋ ሰንቆ ድህነትን
በ “Euro” ጥይት ሊሞክረው የቆረጠ እንጂ የሰላም ተጓዥ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ አገሪቷ ላለፉት አመታት ባለ ሁለት አሀዝ እድገት
አስመዝግባ ከሆነ ይህ በዚች አገር ከመኖር በስደት መኖር ወይም መሞት ይሻላል ብሎ የሚሰደደው ወገኔ በባእድ ሃገር ናፍቆት ምክንያት
ይሆን? ምሁራኖቻችንስ ለትምህርት ልከን የማይመለሡት የሰው አገር ተመችቷቸው ይሆን?
በመጨረሻም የሃገር እድገት ማለት የድንጋይ ንጣፍ ወይም ቁልል ማለት አይደለም፡፡ የአገር እድገት
ማለት የሕዝብ እድገት ማለት ነው፡፡ ከመንገድ እና ከህንጻው በፊት የህዝብ የመኖር ህልውና መረጋገጥ አለበት፡፡ ይህንን ያህል ኪሎ
ሜትር መንገድ ሰራን፣ ዩኒቨርሲቲ ገነባን፣ የዚህን ያህል ህዝብ የመብራት እና ስልክ ተጠቃሚ አደረግን፣ የዚህን ያህል ሜጋ ዋት
የመብራት ሀይል ማመንጫ ገነባን እና የመሳሰሉት ከህዝብ በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡ በረሀብ የሚሞት ህዝብን የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ
መሞከር ቀብርን ከማዳመቅ የዘለለ ጥቅም የለውም፡፡ እንዲሁም በዳቦ እጦት የሚንገላታ ህዝብን የስልክ ተጠቃሚ ለማድረግም መሞከር
መርዶ ከመንገሪያነት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በብርሃን ውስጥ በረሃብ የሚሰቃይን ህዝብ እያዩ ከመሠቃየት እና ከመዋረድ በጨለማ
ጠግቦ የሚድር ህዝብ በብዙ ሺህ እጥፍ ይሻላል፡፡ የምግብ ፍላጎቱን የተሟላ ህዝብ ጤንነቱ የተጠበቀ ነው፡፡ አክሱምን፣ ላሊበላን፣
ፋሲልን የገነባ ትውልድ ጮማ እየቆረጠ እና ወተት እየተጋተ ያደገ ትውልድ ነው፡፡ ያ ትውልድ መንገድ፣ ሆስፒታል እና ዩኒቨርሲቲ
አልነበረውም ግን ያለመንገድ ይጓዛል፣ ያለ ሆስፒታል ጤናውን ይጠብቃል እንዲሁም ያለ ዩኒቨርሲቲ አለም በአግራሞት የሚመለከተውን
ይህ በዩኒቨርሲቲ የተጥለቀለቀ ትውልድ የማይሰራውን ብቻ ሳይሆን የማያልመውን ሥራ ይከውናል፡፡ ስለዚህ ከመሰረተ ልማት ግንባታ በፊት
የህዝብ ግንባታ ይቀድማል፡፡ ህዝብ ደግሞ በሬንጅ፣ በኮብልስቶን እና በብሎኬት አይገነባም፡፡ የህዝብ አቅም በተመጣጠነ ምግብ ነው
የሚገነባው፡፡ ሕጻናትን እንኳን በወተት፣ በእንቁላል፣ በፍራፍሬ፣ በአትክልት እና በስጋ ማሳደግ በማቻልበት በዚህ ወቅት እንዴት
ጤናማ ትውልድ መፍጠር ይቻላል? ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነጋ ጠባ ህጻናትን የተመጣጠነ ምግብ መግቡ እያለ በቴሌቪዥን ይለፈልፋል፡፡
ሕዝቡ ይህንን መች አጣው ያልገባኝ ግን የማይቀመሰው ወጪ በማን ይሆን? የሚያስለፈልፉት እና የሚለፈልፉት በብዙሀኑ ህዝብ እና በእነርሱ
መሃከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀው ያዩት አይመስለኝም፡፡ ገበሬ መስሎ ማስታወቂያ መስራት ወይም ማሰራት እና ገበሬ መሆን የተለያየ
ነው፡፡ እንቁላል ከምግብነት አልፎ ሕንጻ የተገነባበት እንዲሁም ውሃ ለጠማው መንገደኛ ወተት የሚሰጥበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን በክፍያ
እንኳ አልተቻልም፡፡ ለነገሩ እነርሱ ወተት ከየት ይገኛል ቢባሉ ከፍሪጅ ከሚለው የሕብረተሰብ ክፍል ሊሆኑ ስለሚችሉ ወተት ለማግኘት
ፍሪጃቸውን መክፈት ብቻ በቂ ነው፡፡
የሳምንት
ሰው በለን!!
No comments:
Post a Comment