Friday, 21 March 2014

ሞቷል እንቅበረው



የሳው "መንግስት" (መንግስት ብሎ መጥራት ስለሚከብደኝ) በዜጎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ግድያ እና እንግልት ለመቃወም የወገን ስቃይ ስቃያችን በደላቸው ደግሞ በደላችን ነው ብለው አደባባይ የወጡ  ላይ የኢህአዴግ "መንግስት"  (መንግስት ብሎ መጥራት ስለማልችል) ከየትኛውም የመንግስት አይነት በማይጠበቅ ሁኔታ የፈፀመው አፀያፊ እና አሳፈሪ ተግባር የምገልጽበት ቃላት በመፈለግ ላይ ባተኮርኩበት ወቅት ነበር አንድ ተረት ትዝ ያለኝ፡፡ ተረቱን አንዲት ጓደኛዬ ከሰጠችኝን  "ኑሮ እና ፖለቲካ" የሚለው የበሃይሉ /እግዚያብሔር መጽሐፍ ላይ ነበር ያነበብኩት፡፡ እንዲህም ይነበባል… ከሁሉ በፊት ግን ለመጽሐፉን ደራሲ ብሎም መጽሐፉን አነበው ዘንድ ለሰጠችኝን ወዳጄን ከመቀመጫዬ ብድግ እንዲሁም ከወገቤ ጎንበስ ብዬ ምስጋናዬ ማቅረብ ይኖርብኛል፡፡
በአንድ ወቅት ከህግ እና ከደንብ እንዲሁም ከሃገራዊ ጥቅም ውጪ በመንቀሳቀስ የግል ጥቅሙን በሚያሳድድ ግለሰብ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ እና እርምጃ ለመውሰድ ምክር ቤቱ ስብሰባ ይዟል፡፡ የክሱ አቅራቢ "ይህ ሰው እኛ ካበጀንለት ስርዓት ውጪ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ህጋችንን ጥሷል፡፡ ከሃገራዊ ጥቅም ይልቅ ለራሱ ጥቅም እየተጋ ስለሆነ ምን እናድርገው? በሉ አንድ ውሳኔ እንስጥና ወደ ጉዳያችን እንመለስ" በማለት ክሱን አቀረበ፡፡
ከወደ ጥግ አንድ እጅ ተመዘዘ፡፡ "ምን እናደርገዋለን? እርሱ ከህዝብ ይበልጣልን? ማስወገድ ነዋ!!" ሲል ቁጣ በተሞላ አንደበት ተናገረ፡፡ ቤቱ ሃሳቡን ተቀበለው፤ "አዎ እንግደለው! እንግደለው!" ሲልም ተንጫጫ፡፡ "ፀጥታ! ፀጥታ!" የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ቤቱን ስረዓት ለማስያዝ ሞከሩ፡፡ "አዬ! እንዲህ አይነት መናኛ ሰው እያለ ምን ስርዓት አለ? ምንስ ጸጥታ አለ? መግደል ነው፤ መገላገል!!" በማለት ተሰብሳቢው አጉረመረመ፡፡
"አንድ ጊዜ! እባካችሁአንድ ጊዜ!" ከወደ መሃል አንድ እጅ ተመዘዘ፡፡ ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ በሰብሳቢው ጥረት እና ውሳኔ ተፈቀደለትና "አመሰግናለሁ!" በማለት ንግግሩን ጀመረ ቀጥሎም "ሰውዬውን ለመግደል መወሰናችሁ አልገባኝም!" ህዝቡ ግር ተሰኘ፡፡ "እንዴት!" አሉ ጥቂት የማይባሉ ተሰብሳቢዎች በብስጭት፡፡ ተናጋሪው ረጋ ብሎ "ሰውዬው እኮ አስቀድሞ ሞቷል!" አለ፤ ቀጥሎም "ባይሞት ኖሮ የዚህን ማህበረሰብ ክብር የሚነካ ነውር ይፈጽም ነበርን? ባይሞት ኖሮ የዚህ ህዝብ ሰላም ያደፈርስ ነበር? ስለዚህ እኔ የምለው ይገደል ሳይሆን ይቀበር ነው" ሲል ሃሳቡን ቋጨ፡፡
ተሰብሳቢዎቹ ተደሰቱ፡፡ የሚፈልጉት ይህንን ነበርና፣ "ድንቅ ሃሳብ!" ሲሉ አደነቁ፡፡ "ሞቷል እንቅበረው!!" በሚለው ተስማሙ፡፡ ወድያው ሰውዬው ዘንድ የሚሄድ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡
የኮሚቴ አባላት በፍጥነት ትእዛዙን ለማስፈጸም ወደ ሰውዬው ቤት ሄዱ፡፡ በሩንም አንኳኩ፡፡
"አቤት!" አለ ሰውዬው በቡድን የመጡትን ለማወቅ እየተቸገረ፡፡
"የመጣነው ይዘንህ ለመሄድ ነው፡፡"
"የት?"
"ቀብር!"
"ማን ሞተ?"
"አንተ!"
"አልገባኝም!!" ግራ መጋባቱን ለማሳየት ዓይኑን የኮሚቴው አባላት ላይ አንከራተተ፡፡
"ባንተ ላይ ትልቅ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡ በጉባኤውም ሞቷልና ቅበሩት ተብሎ ውሳኔ ተወስኖብሃል፡፡"

ሰውዬው ደነገጠ፤ "ይህ የቂል ውሳኔ ነው! እኔ አልሞትኩም፡፡ እንደ እናንተ እያወራሁ፣ እየተነፈስኩ እንዲሁም እየሄድኩ ነው፡፡ ልትቀብሩኝ አትችሉም!"
"ምን አለ ውሳኔው ላይቀየር ተነስተህ ብትሄድ?"
"አልሄድም! በፍጹም አልሄድም! ከፈለጋችሁ ክሰሱኝ!" በላያቸው ላይ በሩን ዘጋ፡፡

የኮሚቴው አባላት መከሩ፤ "ምን እናድርግ?" ተባባሉ፡፡
"በቃ እርሱ እንዳለው ከስሰን ፍርድ ቤት እንገትረዋ!"
"ምን ብለን?"
"ይኽ ሰው ሞቶ ሳለ እምቢኝ አልቀበርም አለ ብለን"
"እሺ!!"
ሰውዬው አዘነ፡፡ በጠዋት እቤቱ መጥተው "ሞተሃል፤ እንቅበርህ!" ያሉት ሰዎች ሃሳብ እረፍት ነሳው፡፡ ከቤቱ ወጥቶ ወደ ራሱ ሰዎች ገሰገሰ፡፡ ሰበሰባቸውም፡፡

"ወገኖቼ!" አለ ሰውዬው፤ "ወገኖቼ! ጠዋት አንድ መርዶ ሰማሁ"
"የምን መርዶ?"
"ሞተሃል ተባልኩ፤ ተነስ እንቅበርህ! ተባልኩ"
"እንዴት?"
"እኔስ ግራ የገባኝ ምን ሆኖ?" ባዘነ ድምጽ ሰውዬው ተናገረ፡፡
ከመካከላቸው አንዱ ተነስቶ "በጭራሽ አይሆንም!! በጭራሽ! መቼም እኛ ወገኖችህ እያለን ይህ እኩይ እቅድ ይሳካል ብለህ አትስጋ" አለ፡፡ ቤቱ አጨበጨበ፡፡ ሰውዬው ይህ ሁሉ ወገን እንዳለው በማየቱ ደስ ተሰኘ፡፡ እፎይታም ተሰማው፡፡
ሰውዬው ተከሰሰ፡፡ ከከሳሾች መካከል ጥሩ አንደበት ያለው ሰው መናገር ጀመረ "ይህ ሰው የማይገባ ነውር ፈጽሟል፡፡ ለማህበረሰባችን ልማድ እና ክብር እንዲሁም ለእኛ ፍቅር ደንታ የለውም፡፡ በእርግጠኝነት ሞቷል!!" አስረግጦ ተናገረ፡፡
ዳኛው ዛሬ ገና አዕምሮአቸውን የሚፈትን ጉዳይ ገጠማቸው፡፡ "አንተስ ምን ትላለህ?" ተከሳሹን ጠየቁት፡፡ "ክቡር ሆይ!! እነሆ በፊትዎ ቆሜ እንደምን ይጠይቁኛል? ስለ እውነት በቁሜ ሞተሃል መባሌ ትልቅ በደል ነው፡፡"

"ተከሳሽ!"
"አቤት ክቡር ዳኛ!"
"ምስክር አለህ?"
"ለምኑ ክቡር ዳኛ?"
"ስላለመሞትህ!"
"ስላለመሞቴ ምን ምስክር ያስፈልጋል ክቡር ዳኛ!?"
"ነገር በሶስት ምስክር ይፀናል፡፡ ይኸው ነው፡፡"

ሰውየው ደነገጠ፡፡ ውሳኔውን ከወዲሁ ሲያስበው ዘገነነው፡፡ "በቁሜ ልትቀብሩኝ አትችሉም!! በጭራሽ አትችሉም!!" ሲል ጮኸ፡፡

"በላ ምስክር አምጣ!" ዳኛው መለሱ፡፡ ሰውዬው ፊቱን ወደራሱ ሰዎች ዞር ሲያደርግ ከከሳሾች ወገን ተቀምጠው ተመለከታቸው፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ የእያንዳንዳቸውን ስም እየጠራ ምስክር ይሆኑት ዘንድ ጠየቀ ነገር ግን የሁሉም መልስ "የለም! ሞተሃልና በውሽት አንመሰክርም!!" የሚል ሆነ፡፡
ዳኛውም ቁርጥ ያለውን ፍርድ አስቀመጡ "ይህ ሰው እንዳላችሁት ሞቷልና ወስዳችሁ ቅበሩት!!" ውሳኔያቸውንም በፊርማቸው አፀኑ፡፡
እኔም ዛሬ ይህን ተረት በመጠቀም የኢህአዴግን መሞት በሶስት ድርጊታዊ ምስክሮች ላረጋግጥ፡፡
1.      በመንግስት በአግባቡ ያልተጠና የሰፈራ ፕሮግራም ምክንያት ከቦታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የወደቁ ገበሬዎችን ለመርዳት እንቅስቃሴ ያደረጉት አካላት ላይ የድብደባ እና የእስራት ተግባር መፈጸሙ
2.      በአሰቃቂ ሁኔታ 30,000 በላይ ዜጎቻችንን ህይወት ለቀጠፈው ግራዚያኒ ለተባለው የፋሽስት ኢጣሊያን ጦር አዛዥ የኢጣሊያ መንግስት ሃውልት ሊገነባለት አይገባም በማለት ተቃውሞ የወጡ ሰዎች ላይ ድብደባ፣ እንግልት እንዲሁም እስራት መፈጸሙ
3.      በቅርቡ ደግሞ በሳውዲ በስደት የሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የሚደረገው ከልክ ያለፈ እና አለም አቀፍ ህግጋትን የተላለፈ -ሰብዐዊ ድርጊት በመቃወም የሳውዲ መንግስት ከድርጊቱ እንዲታቀብ የታሰሩትም ባስቸኳይ እንዲፈቱ ብሎም ለሞቱ ወገኖቻችን ተገቢውን የደም ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስትም ለዜጎቹ ተገቢውን ክብር በመስጠት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሃገራቸው የመመለስ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ለመጠየቅ የወጣ ህዝብ ላይ ድብደባ እና እስራት ማድረሱ
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቻ ነገሮች የኢህአዴግን ሞት ያስረዳሉ ብዬ ከማስባቸው እልፍ ምስክሮች መካከል የቅርብ ጊዜ ናቸው፡፡
ወያኔ መቼ ሞተ? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን ጊዜ መጥቀስ ባይቻልም አንዳንዶች ከመሪያቸው ሞት ጋር አብሮ ሞቷል ሊሉ ቢችሉም እኔ ግን ከዛም በፊት ነው ባይ ነኝ፡፡ ከዛ በፊት መቼ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ሊያመላክት ወይም ሊጠቁም የሚችለው በክፍፍላቸው ወቅት የቀድሞ መሪያቸው መለስ ዜናዊ "ከአናታችን ወይም ከጭንቅላታችን በስብሰናል!!" ብለው የተናገሩት ነው፡፡
መቼም አንድ ነገር አካሉ ከበሰበሰ (እጅ ወይም እግር ከሆነ) ተቆርጦ ይጣላል፡፡ የበሰበሰው ጭንቅላት ከሆነ ግን ህይወት የለውም ወይም ሞቷል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ወያኔ ከዚህ የተፈጥሮ ህግ ውጪ ከሆነ እና እንደሌላው አካል ጭንቅላቱን አስቆርጦ ህይወት ከቀጠለ ወያኔ ማሰብ እና ማገናዘብ ላለመቻሉ ምክንያት ሊሆን ይችላል ነገር ግን እንደእኔ አመለካከት ወያኔ ያኔ ከክፍፍሉ በፊት ሞቷል፡፡ ስለዚህ ወያኔ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት እየታገለ የነበረው ላለመሞት ሳይሆን ላለመቀበር ነው፡፡
ስለዚህ ቀድሞ በየዘፈኑ መሃል
ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር
አይ ሃገር አይ ሃገር አይ ሃገር ጎንደር፡፡
ይባል የነበረውን ተወዳጅ ግጥም እንዲህ ብዬ ለመቀየር አሰብኩ
ሕግ የለም እንጂ ህግማ ቢኖር
ዳኛም የለም እንጂ ዳኛማ ቢኖር
ፍርድ ቤት መገተር ወያኔን ነበር፡፡
በመጨረሻም የወገን ክብር ማለት የራስ ክብር እንዲሁም የሃገር ፍቅር ማለት የራስ ፍቅር ማለት ነው፡፡ ወገንን አዋርዶ እራስን ማስከበር አይቻልም፡፡ ባለቤት ቀንዱን የሰበረውን በሬ ጎረቤት አይኑን ያጠፋዋል እንደሚባለው እራሳችን ያዋረድነውን ሰው እንዲያከብርልን መጠየቅም አይቻልም፡፡ ህይወት ያለው ሰው ለሃገሩ ፍቅር እንዲሁም ለወገኑ ክብር ይኖረዋል፡፡ ታዲያ እውን ወያኔ የሚታገለው ላለመሞት ወይስ ላለመቀበር? እኔ ላለመቀበር ነው ብያለው እናንተስ?
ለመኖር ባደረገው ጥረት እራሱን የገደለ እንዲሁም ላለመቀበር በሚያደርገው ጥረት የራሱን ጉርጓድ የቆፈረ እንዲሁም በላዩ ላይ ትቢያ የነሰነሰ ከወያኔ ውጪ ማን አለ??? ማንም….      

የነገ ሰው ይበለን!!

No comments:

Post a Comment