Saturday, 22 March 2014

ኢትዮጵያዊነት



አትዮጵያዊነት ለእኔ በቀለበት ይመሰላል፡፡ ቀለበት ፈርጥ ካለው ያምራል፡፡ ያለ ፈርጥ ግን ቀለበት አለ፡፡ ግን አያምርም፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጎሳዎች የቀለበት ፈርጥ እንጂ ቀለበት አይደሉም፡፡ ህልውናቸው ከቀለበቱ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ ቀለበት ከሌለ ፈርጥ የለም፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ እና ሌሎችም እያልን በሃገሪቷ ውስጥ ያሉትን ጎሳዎች በጠቅላላው ብንዘረዝር የሃገሪቷ ውበቶች ወይም ፈርጦች ናቸው፡፡
woyanne's dream
እያንዳንዱ ጎሳ እና የጎሳ አባል ማወቅ የሚገባው ዋና ነገር ጎሳው ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ያገኘው ገፀ-በረከት እንጂ መርጦ እና ፈቅዶ ያገኘው አለመሆኑን ነው፡፡ እኔ ኦሮሞነቴን ወይም አማራነቴን ያገኘሁት ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ነው ብሎ ማሰብም ሆነ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እኔ ኢትዮጵያዊ ባልሆንም ኦሮሞ፣ አማራ ወይም ትግሬ ወይም ሌላ ጎሳ መሆን እችላለሁ የሚል ግንዛቤ እውነትነት የሌለው የትም የማያደርስ መንገድ ነው፡፡ አንዳንድ ያወቅን የነቃን የጎሳ አባላት ነን የሚሉ ‹‹አላዋቂ አዋቂዎች ወይም አለማወቃቸውን የማያውቁ አዋቂዎች›› ማንነታቸውን እና መሰረታቸውን ረስተው የሚያራምዱት መርዘኛ አስተሳሰብ የትም አያደርስም፡፡
እንዴት እና በየትኛው መመዘኛ አሮሞ ኢትዮጵያዊ ከመሆኑ በፊት አሮሞ ሊሆን እንደሚችል ‹‹የኦሮሞ ፈርስት›› አስተሳሰብ ጠንሳሾች እና አራማጆች ማስረዳት የሚያስችል የእውቀትም ሆነ የሞራል ብቃት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እራሳቸው በየጓዳው የሚያበስሉትን መርዝ እንደማስረጃነት ለማቅረብ ሊያስገቡበት የሚችሉበት ምንም ክፍተት የለውም፡፡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ብቸኛው ክፍተት የወያኔ መንግስት ያዘጋጀላቸውን የጎሳ ፖለቲካ ብቻ ነው፡፡ 
እኔ አሮሞነቴ በኢትዮጵያዊነቴ ያገኘሁት ሽልማት እንጂ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ወይም ኢሲያ ወይም የተቀረው አፍሪካ ውስጥ ብወለድ አሮሞነትን የሚያክል ትልቅ ገፀ-በረከት አገኛለሁ ብሎ ማሰብ የቁም ቅዠት ብቻ ሳይሆን እብደትም ነው፡፡ ምናልባት ‹‹የኦሮሞ ፈርስት›› አስተሳሰብ ጠንሳሾች እና አራማጆች በዚህ ሰዓት እኔን ለመሞገት የሚጠቀሙበት ክፍተት ቢኖር በኬኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በዩጋንዳ፣ …ያለው ኦሮሞ ኦሮሞነቱን እንዴት አገኘው ብለው ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ቀለም እና ወረቀት ከማባከናቸው በፊት መልሼ ማለፍ ይኖርብኛል፡፡
በተጠቀሱት አገሮች የሚገኘው ኦሮሞ ‹‹የኦሮሞ ፈርስት›› አስተሳሰብ ጠንሳሾች እና አራማጆች በስደት በአውሮፓ እና አሜሪካ እንደሚኖሩት ሁላ በኢትዮጵያዊነቱ የኦሮሞነት ገፀ-በረከቱን ከተረከበ በኋላ በተለያዩ ገፊ ምክኒያቶች (pushing factors) ሃገሩን ጥሎ በመሰደድ አሁን ባለበት አጎራባች አገሮች ለመኖር የተገደደ ነው፡፡ እዚህ ጋር መርሳት ያልነበረባቸው ጉዳይ እነርሱ ዛሬ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ሆነው የሚያቀነቅኑት የጎሳ ተኮር ፖለቲካ መነሻቸው እዚሁ ኢትዮጵያ መሆኑን ነው፡፡ ለምን አውሮፓዊ፣ አሜሪካዊ፣ … የሆነ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ከምባታ፣ …ሊኖር አልቻለም፡፡ የእነዚህ ሃገሮች ማሕፀን እነዚህን ጎሳዎች ለመፍጠር  ስላልተመረጠ ወይም የሚያስችል አቅም እና ብቃት ስለሌለው ነው፡፡
እነዚህ ‹‹የኦሮሞ ፈርስት›› አስተሳሰብ ጠንሳሾች እና አራማጆች የሚያራግቡት የአባቶቻቸውን ታሪክ ሳይሆን የአባቶቻቸውን ጠላቶች ታሪክ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ የኦሮሞን፣ የአማራን፣ ወይም የትግሬን ህዝብ የበደለ ከየትም ሊመጣ አይችልም፡፡  እውነት እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት አባቶቻቸው በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ እምነት የላቸውም? የኦሮሞ ህዝብ አድዋ ዘምቶ በኢትዮጵያዊነቱ የመጣበትን ጠላት መግቢያ መውጫ አላሳጣም?
ለነገሩ እነዚህ ሰዎች ጎበናን የሚያክል ጀግና እንዲሁም ባልቻን የሚያክል የጦር ገበሬ ኦሮሞነት ሲክዱ ማንነታቸውን ወይም አሮሞነታቸውን ክደዋል፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሃገራችን በታሪኳ ዳግም ልታፈራቸው ያልቻለች ጀግኖች ለኢትዮጵያዊነት ክብር ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው እንዲሁም ውድ ህይወታቸውን ያለማወላወል ገብረዋል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ክብር ሳይኖር የኦሮሞነት  ክብር ሊኖር እንደማችል ቀድሞውኑ ተረድተው ነበር፡፡ አሮሞነት ያለ ኢትዮጵያዊነት ምንም አቋራጭ መንገድ እንደሌለ አበክረው አምነው ነበር፡፡ ‹‹ጅራቷ ያደርሳል ካናቷ›› እንደሚባለው ታዲያ እነዚህ ሰዎች የሚያወሩት እና የሚያቀነቅኑት ኦሮሞነት የአባት የቅድመ-አያታቸውን ወይስ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት ጠላት በሆነው የወያኔ መንግስት ለአገዛዝ እንዲያመቸው ያቀበላቸውን አሮሞነት?
እኔ ይህንን ፅሁፍ ስፅፍ ባልቻ እና ጎበና የሞቱለትን በኢትዮጵያዊነቴ ያገኘሁትን ኦሮሞነት መሰረት አድርጌ ነው፡፡ ለእኔ ባልቻ ኦሮሞ ነው፡፡ ለእኔ ጎበና ኦሮሞ ነው፡፡ ለእኔ የእነዚህን ጀግኖች ኦሮሞነት ክዶ አሮሞነት ሊኖር አይችልም፡፡ አንዳንዶች መለስ እና ግብራበሮቹ (አጫፋሪዎቹ) ካደረሱብን በደል ተነስተው ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ሲያስገቡ የባሰባቸውም ኢትዮጵያዊነታቸውን ሲገፉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ የወያኔዎች ኢትዮጵያዊነት መካድ የራስን ኢትዮጵያዊነት መካድ ነው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ይቅረብም ይራቅ ከእኛ ኢትዮጵያዊነት ጋር የተጋመደ ነው፡፡ የአንዱን ኢትዮጵያዊነት ለመግፈፍ ስንሞክር የራሳችንን እንዳንገፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ማንም ሰው ሲያሰኘው የሚሾመው የሚሸልመው ሲያሰኘው ደግሞ የሚገፈው ማዕረግ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሰው ተፈጥረው ሰው ለማጥፋት ታትረው የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ ከኢትዮጵያ ማሕፀን ተፈጥረው አትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊነት ለማጥፋት ቀን ከሌት ተግተው የሚሰሩ የአስተሳሰብ እና አመለካከት ስህተት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይህ ስህተት ማረም የሚቻለው ኢትዮያዊነትን በመግፈፍ ሳይሆን አመለካከት እና አስተሳሰባቸውን በተሻለ አመለካከት እና አስተሳሰብ ለመተካት ታትሮ በመስራት ነው፡፡
የጎበናንም ሆነ የባልቻን ኦሮሞነት የመግፈፍ ወይም ጥያቄ ውስጥ የማስገባት የሞራል ብቃት ሆነ መብት ያለው አንድም ግለሰብ የለም፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊነታቸው ከኦሮሞነታቸው በልጦባቸው ጥቂቶችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ‹‹ያስቀየመ›› ተግባር ፈጽመው እንኳ ቢሆን ኦሮሞነትን ሊያስገፍፍ የሚችል አንዳችም ተግባር የለም፡፡
የኦሮሞ ህዝብ እንደተቀሩት ህዝቦች እና ጎሳዎች በኢትዮጵያዊነቱ ያገኘው እንጂ ያጣው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ወቅቶች በሃገሪቷ ስልጣን ላይ በወጡ ገዢዎች የኦሮሞን ህዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ሲጨቆን መኖሩ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ይህንን የኦሮሞ ህዝብ በኦሮሞነቱ የተቃጣበት ችግር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነቱ የተቃጣበት ችግር ነው፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ከተቃጣበት ችግር ለማላቀቅ ብቸኛ መፍትሔው የኢትዮጵያን ህዝብ ከባርነት እና ጭቆና ነፃ ማውጣት ብቻ እና ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ወጥቶ የኦሮሞ ህዝብ በባርነት የሚኖርበት ሁኔታ እና ምክኒያት የለም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ገሳዎች ከኢትዮጵያዊነታቸው በሚያገኙት ትሩፋት ልክ የኦሮሞ ህዝብም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
ማንኛውም ጎሳ አማራም ሆነ ትግሬ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከየትኛውም ጎሳ አይበልጥም፤ አያንስምም፡፡ ሁሉም ጎሳዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸው የባለቤትነት ድርሻ እኩል ነው፡፡ ማንኛውም ጎሳ ይህንን አምኖ ከተቀበለ በኢትዮጵያዊነት ላይ ምንም ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም፡፡
የኦሮምን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የሚጠራጠሩ ግለሰቦች እና ስብስቦች ለኦሮሞ ህዝብ ጥፋትን እንጂ ልማትን የሰነቁ አይደሉም፡፡ የኦሮሞን ህዝብ አትዮጵያዊነትን መካድ ለኢትዮጵያዊነት የተዋደቁ የኦሮሞ ጀግኖችን መካድ ማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ባይሆን ኖሮ አድዋ ድረስ ዘምቶ ባልደማ ወይም ባልሞተ ነበር፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አድዋ ድረስ የዘመተው ተገዶ ወይስ አድዋ የኦሮሞ ግዛት ነው ብሎ? በእኔ አመለካከት ለሁለቱም መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ ማለትም የኦሮሞ ህዝብ አድዋ ድረስ ሂዶ የደማውም ሆነ የሞተው ተገዶ ወይም ግዛቱ ስለሆነ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን አደጋ የመጋፈጥ እና የመቀልበስ ኃላፊነት እና ግዴታ እንዳለበት አምኖ ስለተቀበለ ነው፡፡
በመጨረሻም እኔ ኦሮሞነቴን በኢትዮጵያዊነቴ ያገኘሁት ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት የተለየ ኦሮሞነትም የለኝም፡፡ ሊኖረኝም አይችልም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነበርኩ፡፡ ኩሩ ኢትዮጵዊ በመሆኔ ኢትዮጵያ ሃገሬ አሮሞ የሚባል ጎሳ በገፀ-በረከትነት አበረከተችልኝ፡፡ እኔም ይገባኛል ብዬ ተቀበልኳት፡፡ ለሌላው ወንድሜ አማራ፣ ለሌላዋ እህቴ ትግሬ፣ ሌላዋ ወላይታ፣ ለሌሎቹ ደግሞ ሌላ ተበረከተላቸው፡፡ ወደው አክብረው ተቀበሉት፡፡  እኔ ኦሮሞነቴን በማከብረው እና በምወደው ልክ ሌሎች ጎሳዎችን እወዳለሁ፤ አከብራለሁ፡፡ ከእነርሱም የተለየ ማንነት የለኝም፤ ሊኖረኝም አይችልም፡፡ 
እዚህ ጋር ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በጀውራራ አይን ለሚያዩት ለጅዋር እና ለጅዋራዊያን መልክቴን ላስተላልፍ… ኦሮሞ ለመሆን ብቸኛው መንገድ ኢትዮጵያዊ መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን አዋርዶ ኦሮሞነትን ማስከበር አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ብቸኛው መንገድ አፍሪካዊ መሆን ነው፡፡ አፍሪካዊ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊ መሆን አይታሰብም፡፡ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ ኦሮሞነት የለም!!!
ስለዚህ ‹‹ቦይ-ኮት›› ብለህ በነካው እጅህ የአባትህን ታሪክ ባቆሸሸው ወያኔ ላይ ‹‹ቦይ-ኮት ወያኔ›› አውጁበት፡፡ ያለ እዚህ መንግሰት አትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ ክቡር ነው፡፡ ይህም ማለት የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግሬ፣ …ህዝብ ክቡር ነው፡፡   
ክብር ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ይሁን!!
የነገ ሰው በለን!!                

No comments:

Post a Comment