ማንስ አስደፍሮ ማንስ ዘብ ቆመልህ?
ስጋውን አጥንቱን ማን ከሰከሰልህ?
ሞቱን ባንተ ሽሮ ድል አጎናፀፈህ?!
በህይወቴ እያለሁ ጠላት አይደፍርክም፤
ጣሊያን ባንተ ጉያ አይውልም አያድርም፤
ፋሺስት ባንተ መንደር አይምነሸነሽም፤
ብሎ የተመመው ላንተ ሊሞትልህ፤
ላንተ የቆሰለው ላንተ የደማልህ፤
አርነት ያወጀው ድል ያጎናጸፈህ፤
አረ ለመሆኑ ትግሬ ብቻ ነበር?
ወይንስ ጦብያ መላው ድፍን አገር?!
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ ማህተብ አትበጥስ፤
በደም የተፃፈ
ታሪክ አትከልስ፤
አረ ለመሆኑ
ማነው የሞተልህ?!!
ማነው የቆሰለው
ማነው የደማልህ?
አጥንቱን ከስክሶ
ድል ያጎናፀፈህ?!
ቼ!! ብሎ የተመመው ነጋሪት የመታው፤
አንቢልታውን ነፍቶ ፎክሮ የወጣው፤
ጎራዴውን መዞ ጦሩን የሰበቀው፤
አንተ እንዳትደፈር ቃል ኪዳን የገባው፤
ላንተ የሞተልህ ላንተ የተሰዋው፣
መላው ኢትዮጵያዊ ድፍን ሃገሩ ነው?
ወይስ አንድ ጎሳ ብቻውን ትግሬ ነው??
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ ማህተብ አትበጥስ፤
በደም የተፃፈ
ታሪክ አትከልስ፤
አረ ለመሆኑ
ማነው የሞተልህ?!!
አጥንቱን ከስክሶ
ድል ያጎናፀፈህ?!
አድዋ ተናገር ምንድነው ዝምታው?
ትግሬ ብቻ ነበር ላንተ ሲል የሞተው?
ድንበር ያስከበረው ደሙን ያፈሰሰው?
ወይስ መላው ሃገር?!
ሲዳሞ እና ሃረር፤
ወለጋ እና ጎንደር፤
ሸዋ እና ወለየው፤
አሩሲው ጎጃሜው፤
ኢሉባቦር ከፋው፤
ባሌ ጋሞጎፋው
ኤርትራና ትግሬው፤
አልነበር እንዴ ላንተ ሲል የሞተው?!
በዘር ሳይቆጠር ሃይማኖት ሳይፈታው፣
ጥቅም ሳይደልለው ድህነት ሳይረታው፡፡
እምቢኝ ላገር ብሎ እምቢኝ ላንተ ብሎ፤
ሚስት እና ልጆቹን እርግፍ አርጎ ጥሎ፤
እርሻው አይታረስ አረም ይብላው ብሎ፤
አረም እንዳይበቅል ባድዋ ተራራ፤
በጎራዴው አርሶ ጥይቱን የዘራ፤
ጭንቅላት የቀላው በጩቤ በካራ፤
ድሉን ያደመቀው በጀግና ፉከራ፤
ትግሬ ብቻ ነበር?
ወይስ መላው
ሃገር?
አድዋ ተናገር!!
በማተብህ ጽና
ለህሊናህ እደር፡፡
ከሰሜን ከደቡብ ርቀት ሳይገድበው፤
ከምዕራብ ከምስራቅ ጸሃዩ ሳይገታው፤
ሆ! ብሎ የወጣው ላንተ የሞተልህ፤
ሞቱን ባንተ ሽሮ ድል ያጎናፀፈህ፤
አረ ለመሆኑ ትግሬ ብቻ ነበር?
ወይንስ ጦብያ መላው ድፍን አገር?!
አድዋ ተናገር!!
ቃልኪዳን አትፋቅ ማህተብ አትበጥስ፤
በደም የተፃፈ ታሪክ አትከልስ፡፡
ዛሬ ዘመን ከፍቶ አገር ተበትኖ፤
በዘር በሃይማኖት ጎሳ ተሸንሽኖ፤
አገር እበት ወልዳ ትል ደሟን ሲጠባ፤
በባንዳ ታጅቦ ጠላት ቤት ሲገባ፤
አድዋ የኛ ነው! ላንተ ምንህም ነው!
ይሉን ጀምረዋል ጥንቱን እያወቅነው፤
አድዋ ያለ እናቱ፤
አድዋ ያለ ኢትዮጵያ የሙት ልጅ ባንዳ ነው፡፡
አድዋ ተናገር!
በቃል ኪዳና ጽና ለማተብህ እደር፤
በደም የተጻፈ ታሪክ አትሸርሽር፤
ላንተ የሞተልህ ትግሬ ብቻ ነበር?
ወይንስ ጦቢያ መላው ድፍን አገር??
No comments:
Post a Comment