Tuesday, 15 April 2014

እናንተ በፈለጋችሁት ጥሩት!!!



አንዳንዶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰማያዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ ያሰጋቸው ሆድ አደሮች (ሆድ ከሃገር የሰፋባቸው) የመንግስት ካድሬዎች እና አሽከሮች ከጅብ ቆዳ የተሰራ ከበሮ ሁሌም ቢደበድቡት የሚያወጣው ድምጽ ‹እንብላው…እንብላው…› ነው እንዲሉ ‹‹አሸባሪ፣ አክራሪ፣ የቀለም አብዮተኞች፣ የምዕራባዊያን ተላላኪ፣…›› የሚለውን ቃል እየተቀባበሉ ሲያዜሙ መመልከት የእለት ተዕለት ተግባራችን ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሰረተበት እለት አንስቶ ያለ አንዳች ማወላወል ሃገር እና ህዝብን በማስቀደም ሰላማዊ ትግልን እንደ ብቸኛ አማራጭ እየተከተለ እዚህ የደረሰ እና ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠል በሰላማዊ ትግል ብቻ ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ቀን ከሌት ተግቶ የሚሰራ ፓርቲ ነው፡፡
እንኳንስ ህሊናቸውን ለሆዳቸው ባርነት ያስገቡ ሙያ የለሽ ሙያተኞች የተወኑበት በውሸት የተቀነባበረ ዶክመንተሪ ይቅርና እስራት እና ግድያም ቢሆን ከአላማችን ቅንጣት ታክል ዝንፍ እንደማያደርገን ለአምባገነኖች መርዶ ማርዳት እንዲሁም ለፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች የምስራች ማብሰር እፈልጋለሁ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ አሽከር እንጂ የምዕራባዊያን አሽከር አይደለም ወደፊትም ሊሆን የሚችልበት ምንም አይነት ምክኒያት የለም፡፡ ይህንን ‹‹ለባዕዳን አልጋ ለህዝቡ ቀጋ›› የሆነን መንግስት ተብዬ ተቃውመን ፓርቲ የመሰረትን የህዝብ ህመምና ስቃይ የሚያመን እንዲሁም የሃገራችን ውርደት የሚያንገበግበን ሰዎች መሆናችንን እንኳን ህዝቡ እራሱ መንግስት ተብዬው ያውቃል፡፡ እዚህ ጋር ሁሌም የሚገርመኝ ይህ መንግስት ሌሎችን ‹የምዕራባዊያን ተላላኪ፣ በብሄራዊ ጥቅም ላይ የሚደራደሩ፣…› ብሎ የሚጠራበት አፍ እና ድፍረት ይኖረዋል? ከደርግ ጋር ያደረጉትን መራር ተጋድሎ በድል ይወጡ ዘንድ ማን ነበር ያገዛቸው? የሱማሌ ወረራ ጊዜ ዚ-አድባሬ ማንን ነበር የጋለበው? ማን ነበር መንገድ የመራው? ወንድም ህዝቦችን ያለያየ እና ደም ያቃባ እንዲሁም ሃገሪቷን ወደብ አልባ ያደረጋት ማነው?  ገበሬውን ከቀዬው እያፈናቀለ ለባዕዳን መሬቱን አሳልፎ የሰጠው ማነው? በአያት ቅድመ አያቶቻችን ደምና አጥንት ታፍሮ እና ተከብሮ በቀየውን ዳር ድንበር የተደራደረው ማነው? ህዝቡን በጎሳ ከፋፍሎ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት በሃገራችን ዳግም እንዲካሔድ መንገድ በመጥረግ ላይ ያለው ማነው? ጎሳን ከጎሳ እያጋጨ ያለው ማነው? ታዲያ ይህንን ሁሉ ጉድ ይዞ ስለ ተላላኪነት እና ተደራዳሪነት ማውራት ፈጽሞ ይቻላል?     
ሰላማዊ ተቃውሞ ማለት ምርጫ ብቻ ነው ብሎ የሚያምን አካል ካለ የዋህ ብቻ ሳይሆን በዘመን ያልተሞረደ ጅልም ጭምር ነው፡፡ ይህ አምባገነን ስርዓት ዲሞክራሲያዊ ወይም ህገ-መንግስታዊ መብታችንን ብቻ ሳይሆን የነፈገን ሰብዓዊ ነፃነታችንንም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በቅድሚያ ያለምንም ማወላወል እና ማመንታት ነፃነታችንን ለማስመለስ በሰላማዊ መንገድ ማንኛውንም የትግል ስልት ከመጠቀም ፈጽሞ ወደ ኋላ ልንል አይገባም፡፡
የራበው ዳቦ ሲጠይቅ ‹‹አሸባሪ›› የሚል፣ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ ‹‹አክራሪ›› እያለ ዘብጥያ የሚያወርድ መንግስት እንዲሁም ህዝብ ለሚያነሳው ተገቢ የመብት ጥያቄ ሁሉ ‹‹ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት 7፣…›› የሚል ምላሽ የሚሰጥ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን እስር ቤት የወረወረ ስርዓት የሰላማዊ ታጋዮችን ‹‹የቀለም አብዮት አቀንቃኝ፣ የምዕራባዊያን ተላላኪ፣ …ወዘተ›› እያለ ስም ቢያወጣ ከአህያ ምን አይጠበቅም እንደሚባለው ምንም አይደንቅም፡፡
ደርግም እነርሱ ጫካ በነበሩበት ወቅት ‹‹ጥቂት የምዕራባዊያን ተላላኪ›› እያለ የዳቦ ስም ያወጣላቸው እንደነበር የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡ ዛሬም እነርሱ ስንቶች የህይወት መሰዋዕትነት ከፍለው ያገኙትን ስልጣን እና ማይክራፎን ለተመሳሳይ ልፈፋ ቢጠቀሙበት ‹‹ቀድሞም መች የነፃነት ታጋይ ነበሩ?›› የሚለውን ጥያቄ ዳግም እንዲያስተጋባ ያደርጋል፡፡ የአማራን ህዝብ እና የኦርቶዶክስ ተዋክዶ ሃይማኖትን ለማጥፋት ተብሎ የተቋቋመ ድርጅት በየትኛውም መለኪያ ቢለካ የነፃነት ታጋይ ሊሆን አይችልም፡፡ ማንን ከማን ነፃ ለማውጣት?
እንኳን የተቋቋሙለትን የትግራይ ህዝብ ይቅርና እራሳቸውን እንኳን በአግባቡ ነፃ ማውጣት አልቻሉም፡፡ አሁንም እንደቀድሞው የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚዳክር ህዝብ ነው፡፡ ይህን ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ከከፈለው መሰዋዕትነት አንፃር አሁን ያለበት ደረጃ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ይህንን ህዝብ ‹‹ወያኔ የታገለው አንተን ነፃ ለማውጣት ነው?›› ብትሉት ከት ብሎ እየሳቀ ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት ውሃ የሚሞቀው ለገላሽ ነው አሏት›› ብሎ ይተርትባቸዋል፡፡
የቀለምም በሉት የብርሃን፣ የሰይጣንም በሉት የመላዕክት፣ ቀይም በሉት ሰማያዊ አብዮት ማለት ያው አብዮት ነው፡፡ በሃገሪቷ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ፣ የዲሞክራሲያዊ እና ህገመንግስታዊ መብቶች በማን አለብኝነት የሚደፈጠጡበት ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ በማንኛውም ሰላማዊ አብዮት ስልጣኑን ወደ ባለቤቱ (ህዝብ) ለመመለስ ተግተን ከመስራት ወደ ኋላ ማፈግፈግ አይታሰብም፡፡         
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግል የነፃነት ትግል ነው፡፡ እኔ ደግሞ እንደግለሰብ ዲሞክራሲያዊ መብቴን እንጂ ነፃነቴን ከምርጫ ኮሮጆ አልጠብቅም፡፡ መጀመሪያ ምርጫ ኮሮጆ ድረስ በኩራት የሚያራምድ ነፃነት ያስፈልገኛል፡፡ ያለ ነፃነት ወደ ምርጫ ኮሮጆ መራመድ አይቻልም፡፡       

No comments:

Post a Comment