Monday, 14 April 2014

መተሳሰብ-መከባበር-መተባበር-መዋሃድ የፖለቲካችን የ‹‹መ›› ህጎች



ይህ የአገዛዝ ስርዓት ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት እንደ ሰርከስ ትርኢት በክር ላይ እየተራመደ በስልጣን ኮርቻ ላይ ይቆይ ዘንድ ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደረገው የስርዓቱ ጥንካሬ ሳይሆን የአማራጭ የተፎካካሪ ድርጅቶች ድክመት ነው፡፡ የዝንጀሮን መንጋ አንድ ውሻ ይበትነዋል እንደሚባለው ይህ ስርዓት የሚበታትነው ጠንካራ እና ታማኝ ውሻ ያጣ በየማሳው የሚንጎማለል ሰብል አውዳሚ የዝንጀሮ መንጋ ነው፡፡ ዝንጀሮው ያለምንም ፍራቻ ሰብል ያወድም ዘንድ ያደረገው ማህበረሰቡ ታማኝ እና ጠንካራ ውሻ መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡
ማህበረሰቡ በምርጫ 97 ጠንካራ ውሻ በመፍጠሩ ዝንጀሮዎቹ ብትንትናቸው ቢወጣም ወሾቹ ጠንካራ እንጂ ታማኝ ባለመሆናቸው ዝንጀሮዎቹ ዳግም ተሰባስበው የሰብሉን ማሳ ተቆጣጠሩት፡፡ ይኸው እስከ አሁን ድረስ እኛ ስናርስ፣ ስንዘራ፣ ስናርም… እነርሱ ደግሞ ሰብሉን ሲያጋብሱ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ፖለቲካችንም የዝንጀሮውን መንጋ ይበትነው ዘንድ፣ የሰብሉንም ማሳ በአስተማማኝ ቁጥጥር ያውል ዘንድ እና ከዳግም የዝንጀሮዎች ወረራ ለመከላከል መተሳሰብ-መከባበር-መተባበር-መዋሃድ የሚባሉ የ‹‹መ›› ህጎች ያስፈልጋሉ፡፡     
በሃገራችን ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የመተሳሰብን፣ የመከባበርን፣ የመተባበር እንዲሁም የመዋሃድን አስፈለጊነትና ጠቀሜታን የማይረዳ ከኢህአዴግ ውጪ ያለ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲታሰቡ በቅድሚያ ፖለቲከኞቻችን ‹‹የግል ፍላጎትና ስሜታቸውን በመግራት የሐገርን ጉዳይ አስቀድመው፣ ከሥልጣን በላይ ትውልድ ተሻጋሪ ለውጥን አልመው፣ ሲሆን ተዋህደው አንድ ሁለት በመሆን ካልተቻለም ተደጋግፈውና ተባብረው እንዲታገሉ›› (በታምራት ታረቀኝ፤ ለውጤታማ ትብብር ካለፈው መማር በሚል ርዕስ በሰማያዊ ፓርቲ ከቀረበ ጥናታዊ ፅሑፍ የተወሰደ) በተለያዩ ወቅቶች ከጀማሪ ፖለቲከኛ እስከ የፖለቲካው ሊቃውንት እንዲሁም ከህብረተሰቡም ሳይቀር ጥሪ ሲቀርብ መስማት የተለመደ ነው፡፡
የፓርቲዎችን ውህደት አንዳንዶች በቅንነት እና አርቆ በማሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አስከፊ እና አፀያፊ ስርዓት ለመለወጥ እንደ ብቸኛ አቋራጭ መንገድ ተመልክተው ጉዳዩን ሲያራግቡት ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በውስጣቸው ያለው የነፃነት ናፍቆት እረፍት ቢነሳቸው ይህንን የሃገር እና የታሪክ ነቀዝ መንግስት ለአንድ ሃገር በአንድ አላማ ተሰልፈን በአንድ አቅጣጫ ደብድበን እንጣለው ቢሉ አይፈረድባቸውም፡፡
ፓርቲዎች የሚታገሉት አንድ ስርዓት፣ የሚታገሉላት አንድ ሃገር እንዲሁም የሁሉም አላማ በኢኮኖሚ እና በዲሞክራሲ የተሻለች አንድነቷን የጠበቀች የህዝቦችዋ እኩል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማህበራዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት ሃገር መፍጠር ነው፡፡ ይህ ለፓርቲዎች መተሳሰብ፣ መከባበር እና መተባበር ዋነኛ መሰረት ሊሆን ይገባል፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ፓርቲ ይህንን አምባገነን ስርዓት አስወግዶ የተነሳለትን አላማውን ከግብ ለማድረስ የየራሱ አማራጭ መንገድ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይገባልም፡፡
ሁሉም የመንግስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ አይነት ርዕዮተ አለም የሚያራምዱ እንዲሁም ተመሳሳይ የትግል ስልት የሚጠቀሙ መሆናቸው ለመንግስት ተብዬው የጭቆና ጊዜን ከመግዛት የዘለለ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ተቃዋሚዎች አንድ በሚያደርጋቸው ነገር ላይ እየተባበሩ እንዲሁም በሚያለያያቸው ላይ እየተከባበሩ ትግላቸውን በማፋፋም ይህንን ጨቋኝ ስርዓት እንደሰደድ እሳት መያዢያ መጨበጫ ሊያሳጡት ይገባል፡፡ ብልህ እና ጠንቃቃ እንቁላል ነጋዴ ሁሉንም እንቁላሉን በአንድ ቅርጫት ውስጥ አያስቀምጥም፡፡ ይህንን ስል ግን በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ሃገር አቀፍና የጎሳ ፓርቲዎች እንዲሁም ፓርቲ ነን ባዮች በጠቅላላው መኖራቸው ተገቢ ነው እያልኩ አለመሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡
በተለይ በሃገራችን ውስጥ አንድን ጎሳ ያነጣጠረ ልማትም ሆነ ውድመት በግሌ አለ ብዬ ስለማላስብ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች በተቻላቸው ፍጥነት ከሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር በመዋሃድ አልያም እራሳቸውን ወደ ብሔራዊ (አገር አቀፍ) ፓርቲ ከፍ (upgrade) በማደረግ የሃገሪቷን ፖለቲካ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች በፖለቲካው ውስጥ ጠንክሮ ለመቆየት ያላቸው አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፡፡ ዋነኛው ከብሔራዊ ፓርቲዎች ጋር መዋሃድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ እራሳቸውን ወደ ብሔራዊ ፓርቲ ደረጃ ከፍ ማድረግ፡፡      
እያንዳንዱ ፓርቲ ከውህደት በፊት አብሮ ተከባብሮና ተባብሮ በመስራት ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ ፓርቲዎች ተቀራርበው እና ተከባብረው መስራት እንኳን ባልቻሉበት ሁኔታ ውህደትን ማሰብ ህዝቡን ተስፋ ከማስቆረጥ የዘለለ ፈይዳ ይኖረዋል ብዬ በግል አላስብም፡፡ ለአንዲትም ቀን ተከባብረው አንድም ስራ ተባብረው አብረው መስራት ያልቻሉ እንዲሁም አንዳቸው በአንዳቸው ችግር የሚዝናኑ ፓርቲዎች እና ፓርቲ ነን ባዮች እንዴት በውህደት አንድ ለመሆን ያስባሉ? እርስ በእርስ ሳይጠናኑ እና ሳይተዋወቁ የሚደረግ ጋብቻ ይመስል ውህደትን የፓርቲዎች ህልውና ማረጋገጫ መሆን ይኖርበታል ብዬም አላስብም፡፡ የፓርቲዎች ህልውና መረጋገጥ ያለበት በያዙት ፕሮግራም፣ በሚከተሉት የትግል ስልት እንዲሁም በሚከተላቸው አባላት እና ደጋፊ ቁጥር ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል፡፡
በሃገራችን ውስጥ በተቃውሞው ጎራ ለመሰለፍ እልፍ አዕላፍ ምክኒያቶች ቢኖሩም ለእያንዳንዱ ችግር ፓርቲ ማቋቋም ተገቢም ትርፋማም አይደለም፡፡ ፓርቲዎች መብዛት የተለያዩ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦች የሚራመዱበት መድረክ ከማግኘት አንፃር ከታየ የሚበረታታ ቢሆንም አሁን በሃገራችን እንዳለው እጅግ ከልክ ያለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ለአላስፈላጊ የሰው ሃይል እና የገንዘብ ብክነት ከመዳረግም በተጨማሪ በምርጫ ወቅት ለህዝብ ድምፅ ብክነት መዳረጉ የአደባባይ እውነታ ነው፡፡
በሃገራችን ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ ተቋማት በማከባበርም ሆነ በማተባበር ላይ አጽንኦት ሰጥቶ መስራት የሃገሪቷን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ህብረተሰቡን ከድህረ-ምርጫ 97 ቁዘማ ሊያባንነው ይችላል፡፡ ከምርጫ 97 ወዲህ ህብረተሰቡ በተቃዋሚዎችም ሆነ በመንግስት ላይ እምነት እንደሌለው በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይቷል፡፡
ይህንን ከሁሉም ጎራ በተቃራኒው ተሰልፎ ጉዳዩ በዝምታ እና በቸልታ በመመልከት ላይ ያለውን ህብረተሰብ ዳግም ወደ ተነቃቃ የፖለቲካ ተሳትፎ ለመመለስ ዋነኛ እስትራቴጂ መሆን የሚገባው በመከባበር፣ በመተሳሰብ እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ ከልዩነት በላይ በሃገራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ የትብብር መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
አንዳንዶች የተለያየ ሃሳብን ለማስወገድ ወህደትን ሲደግፉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ የተለያየ ሃሳብ የማይራመድበት መድረክ ለመፍጠር የምንሰራ ከሆነ ከዚህ ስርዓት የተሻለ ስርዓት መፈጠር አይቻልም፡፡ የዚህ ስርዓት አንዱ አስከፊ ገጽታ የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ መንፈጉ ነው፡፡ ሃገሪቷ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምራትን የምናስብ ከሆነ ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብም ሳይቀር በክብር እና በነጻነት የሚንሸራሸርበት ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር የሚችል እና መኖርም ያለበት የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ ግብዓት ነው፡፡ ልዩነት የሌለበት ስርዓት ለመፍጠር መሞከር ጨቋኝን በሌላ ጨቋኝ ከመተካት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት አሁን ላለበት ስህተት የዳረገው የጎሳ ልዩነትን ለማስፋት የአስተሳሰብ ልዩነትን ለማጥፋት የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው፡፡
በአንድ ሃገር ውስጥ ጤናማ የዲሞክራሲ ስርዓት አለ ለማለት አስተሳሰቦች በነጻነት እኩል የሚራመዱበት መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አማራጭ አስተሳሰቦች ህዝብ ጋር ይደርሱ ዘንድ እኩል የሚዲያ ተጠቃሚነት ሊኖርም ተገቢ ነው፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ትግሉን የዲሞክራሲ ሳይሆን የነጻነት ትግል ያደርገዋል፡፡
የተቃውሞ ፖለቲካችን እንዲጠናከር ከተፈለገ መደረግ ያለበት የአስተሳሰብ ልዩነት አክብሮ፣ በአንድነት ላይ በመተባበር እና መሰረታዊ ልዩነት ከሌለ ደግሞ ተዋህዶ አብሮ መቀጠል ሲቻል ነው፡፡ በፓርቲዎች መካከል ከመዋሃድ በላይ ፍፁም መተሳሰብ፣ መከባበር እና መተባበር ሊኖር ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግል ከዲሞክራሲ ትግል በበለጠ የነፃነት ትግል ነው፡፡ የተናጥል ነፃነት ሊኖር አይችልም፡፡ ሊኖርም አይገባም፡፡
በመጨረሻም በሃገራችን ውስጥ ያለው አሰቃቂ እና አሳፋሪ የመብት ጥሰት ያበቃ ዘንድ ሁላችንም ከራስ በላይ ስለሃገር እና ስለወገን በማሰብ ልዩነትን በማቻቻል መከባበር እንዲሁም መተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ባል እና ሚስት እቤታቸው የገባችውን አይጥ ለመግደል ይሯሯጣሉ፡፡ ብልኋ አይጥ ካልጠፋ ቦታ ሄዳ ምጣዱ ላይ ጉብ አለች፡፡ ሚስት የዘረጋችውን በትር ሰበሰበች፡፡ ባል ‹‹ምነው?›› ቢል የሚስት መልስ ‹‹ስለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ›› የሚል ሆነ፡፡ ዛሬ እንዲህ አይነት የፖለቲካ መሪ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ አምባገነኖችን በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ በመተባበር ሲሆን ሲሆን ደግሞ በመዋሃድ ማስወገድ ይቻላል፡፡ ፓርቲዎች አንድም ቀን ሳይተሳሰቡ፣ ሳይከባበሩ እና ሳይተባበሩ ወደ ውህደት የሚደረግ ጉዞ ቆም ብሎ ‹‹ምን ተይዞ?›› ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ከማብቃቴ በፊት የፓርቲዎችን ውህደት ለማስተባበር እንቅስቃሴ ላይ ላሉ ምሁራን ያለኝን አድናቆት እና ድጋፍ እየገለጥኩ ከውህደት በፊት ፓርቲዎች የጋራ ችግራቸው ለመፍታት አብረው የሚሰሩበትን መድረኮች በመፍጠር ፓርቲዎች እርስ በእርስ እንዲተሳሰቡ፣ እንዲከባበሩ ብሎም እንዲተባበሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የነገ ሰው ይበለን!!!    

No comments:

Post a Comment